AMN – የካቲት 30/2018 ዓ.ም.
ከተማ የሕንጻዎች ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ ተስፋና ትጋት የሚወለድበት ሰፊ ዓለም ነው። በከተሞች ጎዳና ላይ የሺህዎች ሕልም ይሸመናል፤ በሕንፃዎቻቸው ጥላ ሥርም የታሪክና የሥልጣኔ አሻራዎች ያርፋሉ። እያንዳንዱ ከተማ የራሱ የሆነ የልብ ትርታ ያለው ሲሆን፣ ነዋሪዎች ደግሞ ያንን ትርታ ሕያው የሚያደርጉ የከተሞቹ ነፍሶች ናቸው።
ከተሞችን የሚገነቡት የሰው ልጆች ቢሆኑም፣ ከተሞችም መልሰው የሰው ልጆችን ማንነትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርጹ የጥበብ ማዕከላት ናቸው።
ዛሬ በከተሞች ቅኝታችን፣ ከአውሮፓ ከተሞች መካከል በተፈጥሮ ውበት፣ በሳይክልና በእግረኛ መንገድ ምቾት እንዲሁም በቱሪዝም ቀዳሚ የምትባለውን የዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሃገንን እናስተዋውቃችሁ።
የነጋዴዎች ወደብ
የኮፐንሃገን ታሪክ የሚጀምረው በ12ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በኤጲስ ቆጶስ አብሳሎን አማካይነት በተመሠረተችው አንድ የባሕር ላይ ምሽግ ነው። በወቅቱ ስሟ “ኮፕማንሃቭን” (Køpmannæhafn) ሲሆን ትርጓሜውም “የነጋዴዎች ወደብ” ማለት ነበር።
ከተማዋ በባሕር ዳርቻ ላይ በመገኘቷ ለዓሣ ማጥማድና ለንግድ ምቹ በመሆኗ በፍጥነት ማደግ ችላለች።

በ17ኛው ክፍለ ዘመን የከተማዋ ዋና መሐንዲስ ተብለው በሚጠሩት ንጉሥ ክርስቲያን 4ኛ ዘመን ኮፐንሃገን ዘመናዊ መልክ መያዝ ጀመረች። ዛሬ ላይ ለቱሪስቶች ቀዳሚ መዳረሻ የሆኑት እንደ ኒሃቭን (Nyhavn) ያሉ ውብ የውኃ ዳርቻ ቦዮችና ታሪካዊ ሕንጻዎች የዚሁ ጥንታዊ ሥልጣኔ ውጤቶች ናቸው።
የእግረኛ መንገድ አብዮት
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ስትናወጥና ብዙ ከተሞች ለመኪናዎች ቅድሚያ ሲሰጡ፣ ኮፐንሃገን ግን የተለየ መንገድ መረጠች። በ1962 ዓ.ም “ስትሮጌት” (Strøget) የተባለው የከተማዋ ረጅም መንገድ ለመኪና ዝግ ሆኖ ለእግረኞች ብቻ እንዲከፈት ተደረገ።
ይህ ትግበራ በወቅቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ ዛሬ ግን የከተማዋ የንግድና የቱሪዝም የልብ ትርታ በመሆን ለተቀረው ዓለም የማይታለፍ ምሳሌ ሆኗል።

አዲስ አበባም አሁን ላይ በኮሪደር ልማት እያከናወነችው ያለው የሳይክል መሠረተ ልማት፣ በከተማዋ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነስ ባለፈ፣ ወደፊት ከቀላል ባቡርና ከሕዝብ ትራንስፖርት ጋር ተቀናጅቶ ለነዋሪዎች ምቹ አማራጭ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ ይገኛል።
የሳይክል መዲና እና የአረንጓዴነት ተምሳሌት
በኮፐንሃገን ጎዳናዎች ሳይክል መንዳት ልክ እንደ ዕለታዊ ምግብ የተለመደ ባሕል ነው። ከተማዋ ለሳይክል ተጓዦች ተለይተው የተገነቡ ሰፊ የመንገድ መሠረተ ልማቶች አሏት። በአሁኑ ወቅት ከ60% በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ለሥራና ለትምህርት የሚንቀሳቀሱት በሳይክል ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ኮፐንሃገን “አረንጓዴ ከተማ” ለመሆን በምታደርገው ጥረት እንደ “ቲቮሊ ጋርደን” ያሉ ጥንታዊና ዘመናዊ መዝናኛዎችን የያዙ ፓርኮችን በከተማዋ መሃል ገንብታለች።

የባሕር ዳርቻ ውሃዋ ንጽሕና ደግሞ ቱሪስቶችና ነዋሪዎች በከተማው መሃል እንዲዋኙና እንዲዝናኑ ዕድል ፈጥሯል።
ይህ ተሞክሮ በአዲስ አበባም በተግባር እየታየ ነው። በአሁኑ ወቅት የወንዝ ዳርቻ ልማቶችና አዳዲስ ፓርኮች የከተማዋን ገጽታ ከመቀዬር ባለፈ፣ ነዋሪዎች በንጹሕ አየር ውስጥ እንዲንቀሳቀሱና የተፈጥሮ ወንዞች ዳርቻዎች ለከተማዋ ተጨማሪ የቱሪዝም ገቢ ማስገኘት ጀምሯል።
ኮፐንሃገን እና አዲስ አበባ
የኮፐንሃገን ተሞክሮ ከተማ ማለት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ ምቹ ማድረግ እንደሆነ ያስተምረናል። ታዲያ ከተመሠረተች 130 ዓመታትን ያስቆጠረችው መዲናችን አዲስ አበባም፣ አሁን ላይ ይህንን የቤት ሥራ በስፋት እየሠራች ትገኛለች።
ቀደም ሲል ነዋሪዎችና ቱሪስቶች በአቅራቢያቸው ለማለፍ የሚሳቀቁባቸው ወንዞችና ለመኪና ብቻ ክፍት የነበሩ ጠባብ መንገዶች ዛሬ ታሪካቸው ተቀይሯል። በኮሪደር ልማት አማካይነት የተገነቡ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መሠረተ ልማቶችና የቱሪስት መዳረሻዎች አዲስ አበባን እነኮፐንሀገን ከደረሱበት ዓለም አቀፍ ከፍታ ላይ እያደረሳት ይገኛሉ።
በያለው ጌታነህ