የዓለም ዓይኖች አዲስ አበባ አበባ ላይ ናቸዉ !

You are currently viewing የዓለም ዓይኖች አዲስ አበባ አበባ ላይ ናቸዉ !

AMN- ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም

የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ ፤ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ ኤምባሲዎች መገኛ የሆነችው አዲስ አበባ ከጥቂት አመታት በፊት የአፍሪካ ህብረት ጉባዔን የመሰሉ አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡

እነዚህ ጉባዔዎች በአመታት መካከል የሚካሄዱ ከመሆናቸዉም በላይ በጉባኤዎቹ ላይ የሚሳተፉ ታዳሚዎች ቁጥርም የተወሰነ ነበር፡፡

በመዲናዋ ሲካሄዱ የነበሩት የኩነቶችም ከስብሰባዎችና መሰል መርሃ ግብሮች የዘለሉ አልነበሩም፡፡

አዲስ አበባ የኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎችን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ ባስመዘገበችዉ ፈጣን ልማት እና እድገት ይህ ታሪክ ተቀይሯል፡፡

በአመታት መካከል ሲካሄዱ የነበሩት አህጉርና አለም አቀፍ ጉባኤዎች አሁን ላይ በወራትና በሳምንታት መካከል መካሄድ ጀምረዋል፡፡

በቀናት ልዩነት የተለያዩ ኩነቶችን ማስተናገድም ሰርክ ሆኗል፡፡

በጥቂት ስብሰባዎችና መሰል ጉባኤዎች ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረዉ የኩነቶች አይነትም አሁን ላይ በፈጣን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች፤ በቱሪዝም ፤ በአለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች፤ በአህጉርና አለም አቀፍ የንግድና ኢንዱስትሪ ትርዒትና ባዛሮች፤ በአህጉርና አለም አቀፍ ልምድ ልውውጦች፤ በሲምፖዚየሞች እና መሰል ታላላቅ ኩነቶች ተተክቷል፡፡

በነዚህ ኩነቶች ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ታሳታፊዎች ቁጥር በፊት ከነበረዉ ከእጥፍ በላይ የጨመረ ሲሆን ታላላቅ የአለም መሪዎችን፤ ቱሪስቶችን፤ አለም አቀፍ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን፤ ታዋቂ ባለሃብቶችን፤ አርቲስቶችን፤ አትሌቶችን፤ ጋዜጠኞችን፤ስፓርተኞችን ፤ ዩቲዩበርና ቲክቶከሮችን እና መሰል ግለሰቦችን አዲስ አበባ ላይ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡

እነዚህ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ማህበራዊ ሚዲዎችን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አዲስ አበባን ለተቀረው አለም የሚገልጡ በመሆናቸዉ የአለም ዓይኖች ዘወትር አዲስ አበባን እንዲመለከቱ ምክንያት ሆኗል፡፡

“አዲስ አበባ በፈጣን እድገት ላይ ነች፤ መዲናዋ እጅግ በጣም ታምራለች፤ ህዝቦቿም ደግና እንግዳ ተቀባዮች ናቸዉ፤ አዲስ አበባ በሰላማዊነቷ ወደር የማይገኝላት መዲና ነች” እና መሰል አስተያየቶችን መዲናዋን ከጎበኙ የዉጭ ሃገራት ዜጎች መስማት የተለመደ ሆኗል።

አህጉርና አለም አቀፍ ኩነት አዘጋጆችም የተለያዩ ጉባኤዎችንና መሰል ዝግጅቶችን ለማካሄድ አዲስ አበባን ቀዳሚ ምርጫቸው ያደረጉ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በመዲናዋ የሚገኙ ትላልቅ የስብሰባ ማዕከላት፤ ሆቴሎች፤ የቱሪዝምና ትራንስፓርት አገልግሎት ሰጪዎች እና መሰል ደርጅቶች እንግዶቹን በመቀልና በማስተናገድ ተጠምደዋል፡፡

ይህም የአዲስ አበባን ብሎም የሃገሪቱን አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ይበልጥ ከማሳለጥ፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ከማጠናከር እና የሃገር ገጽታን ከመገንባት ረገድ ያለዉ ጠቀሜታ እጅግ የጎላ ነው፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review