AMN- መጋቢት 03/2018 ዓ.ም
የ2025/26 ውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ዙር ላይ ይገኛል። 16 ክለቦች በሚሳተፉበት በዚህ የጥሎ ማለፍ ዙር እንግሊዝ በስድስት ክለቦች ተወክላለች።
የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙሩ ሲከናወን ከስድስቱ አንዳቸውም ድል አላስመዘገቡም። የሊጉ መሪ አርሰናል በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ወጥ ብቃት ማሳየት የተሳነው ባየር ሊቨርኩሰንን ገጥሞ 1ለ1 ተለያይቷል።
በሊጉ የአርሰናል የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነው ማንችስተር ሲቲ በሪያል ማድሪድ ብልጫ ተወስዶበት 3ለ0 ተሸንፏል። ቼልሲም የፓሪሰን ዠርማ ክንድ ቀምሷል። የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በስህተት በታጀበው ጨዋታ 5ለ2 ተረቷል።

በታሪኩ አስከፊውን ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርስም በአትሌቲኮ ማድሪድ ተቀልዶበታል። ኢጎር ቱዶርን ቀጥሮ የባሰ የቁልቁለቱን ጉዞ የተያያዘው ቶተንሃም በአትሌቲኮ የ5ለ2 ሽንፈት ገጥሞታል።
ሊቨርፑልም ቢሆን ከመሸነፍ አልዳነም ፤ የመርሲሳይዱ ክለብ በጋላታሳራይ 1ለ0 ተሸንፏል። ከሌሎች የተሻለ ብቃት ያሳየው እና እስከመጨረሻው የተፋለመው ኒውካስትል ዩናይትድ ከባርሰሎና ጋር አቻ ተለያይቷል።
ስድስቱም ክለቦች ውጤቱን ሊቀለብሱት ይችላሉ። በተለይ ከኒውካስትል ውጪ አምስቱ የመልሱን ጨዋታ የሚያከናውኑት በሜዳቸው ነው። ማንችስተር ሲቲ ፣ ቶተንሃም እና ቼልሲ በሦስት ግብ ልዩነት መሸነፋቸው ግን ውጤት የመቀልበስ ሂደቱን የሚያከብድባቸው ይመስላል።
በጥሎ ማለፍ ውስጥ ካሉ ስድስቱ የእንግሊዝ ክለቦች ስንቱ ወደ ሩብ ፍፃሜ የመግባት እድል አላቸው? በመልዕክት ማስቀመጫው ሃሳብዎን ያካፍሉን።
በሸዋንግዛው ግርማ