AMN- ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ በፓሪሰን ዠርማ ከተሸነፈ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ቁጭ ብሏል። ብስጭቱ ከፊቱ ይነበባል። ክለቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለማሸነፍ በጣም ቀርቦ በማጣቱ ውስጡ ነዷል።
ስፔናዊው አሰልጣኝ ዳግም የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ተፋላሚ ሆኖ ዋንጫውን ለማንሳት መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናገረ። ” ከዚህም በላይ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መድረስ አለብን ፤ በዝውውር መስኮት በጣም ትልቅ መመኘት አለብን ፤ ፈጣን እና ብልህ መሆንም ይጠበቅብናል።” ሲል ተናገረ።
አርሰናል አሰልጣኙ ከወራት በፊት ባለው ልክ በዝውውሩ እየተንቀሳቀሰ አይገኝም። በእርግጥ አርሰናል ምኞቱን ብልሃት በተሞላበት መልኩ ለማስኬድ ገና ጊዜ አለው።

ከ22 ዓመታት በኋላ የሊግ ዋንጫ ያመጣላቸው ሚኬል አርቴታ በፈለገው ልክ ግን የዝውውር ሂደቱ እየፈጠነ አይገኝም። የሰሜን ለንደኑ ክለብ የዝውውር እንቅስቃሴ በተለይ ማንችስተር ሲቲ ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ቼልሲ ባደረጉት ልክ አይለካም።
የውድድር ዓመቱ ሊጀምር ከ20 ብዙም የልበለጡ ቀናት በቀረበት በዚህ ወቅት የአርሰናል ፈራሚዎች ሁለት ናቸው። የመስመር አጥቂው ክሪስቶስ ዞሊስ ከክለብ ብሩጅ እንዲሁም በሊድስ ዩናይትድ ውሉ ተጠናቆ የለቀቀው ግብ ጠባቂ ኢላን ሚሌይ የመድፈኞቹ ቤተሰብ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው።
የቴሌግራፍ ፀሃፊ ሳም ዲን ባሰፈረው ፅሁፍ ሚዛናዊ የሆኑ ደጋፊዎች የዝውውር መስኮቱ ገና በመሆኑ መረጋጋትን ይመርጣሉ። በተለይ የዓለም ዋንጫ በመጠናቀቁ ከዚህ በኋላ ያለውን እንቅስቃሴ ማየት ይፈልጋሉ ሲል ፅፏል።
አንዳንዶች ደግሞ አርሰናል የሊግ ዋንጫ እንደማሸነፉ እንደሌሎቹ ክለቦች ቀዳዳው ብዙ አይደለም ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። እንደ ሳም ዲን ከሆነ እነዚህን ደጋፊዎች ሊያስጨንቃቸው የሚገባ አንድ ጉዳይ ግን አለ። ሁለት አጥብቆ የፈለጋቸውን ተጫዋቾች አጥቷል።
የሚኬል አርቴታ ቡድን ከሌስተር ሲቲ ጀርሚ ሞንጋን ለማስፈረም ወራትን ፈጅቶ ማሳካት አልቻለም። ተጫዋቹ ወደ ማንችስተር ሲቲ አምርቷል። እንግሊዛዊው የመስመር አጥቂ ገና የ16 ዓመት ታዳጊ ቢሆንም አርሰናል በጥብቅ ፈልጎት ነበር።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ሞርጋን ሮጀርስን በቼልሲ ተነጥቋል። ሚኬል አርቴታ አጥብቆ የፈለገውን የ24 ዓመቱን ተጫዋች በግሉ እስከማናገር ቢደርስም ዝውውሩ አልተሳካም።

ሁለቱ ተጫዋቾች ወደ ኤምሬትስ ያለመምጣታቸው ትልቅ ምክንያት የዝውውር ገንዘባቸው መናር ነው። አስቶንቪላ ሞርጋን ሮጀርስን በ117 ሚሊየን ፓውንድ ሊሸጥ እንደተቃረበ ለአርሰናል ቀድሞ አሳውቆ ነበር። የአርሰናል ባለስልጣናት እኛም እንፎካከራለን ከማለት ይልቅ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቹህ ነው ያሏቸው። ለሮጀርስ ከ90 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ማውጣት በእቃዳቸው አላካተቱትም።
አርሰናል በአማራጭ ደረጃ የያዛቸው ሳንድሮ ቶናሊ እና ማቴኡስ ፈርናንዴዝ ወደ ቶተንሃም ሆትስፐርስ አቅንተዋል። ሁለቱ ተጫዋቾች በድምሩ 185 ሚሊየን ፓውንድ ማስወጣታቸው ለአርሰናል ለማመን የሚከብድ ሆኗል።
በዚህ ሁኔታ አርሰናል የፈለጋቸውን ተጫዋቾች እንዴት ሊያገኝ ይችላል? ይህ በጣም አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። አርቴታ የኒውካስትሉ አማካይ ቡርኖ ጉማይሬሽ እንዲመጣለት እየገፋ እንደሚገኝ በርካታ የእንግሊዝ ብዙሃን መገናኛ እየዘገቡ ይገኛሉ።
ኒውካስትል ዩናይትድ አምበሉን መሸጥ አይፈልግም። ግዴታ ከሆነበትም ከሳንድሮ ቶናሊ ያገኘውን 100 ሚሊየን ፓውንድ ከጉማይሬሽ ዝውውርም ይፈልጋል። ቢበዛ 70 ሚሊየን ፓውንድ ለማውጣት የተዘጋጀው አርሰናል የ28 ዓመቱን ተጫዋች ፊርማ ለማግኘት ሌላ ፈተና ይጋፈጣል።
የቦርንማውዙ አሌክስ ስኮትም ቢሆን ከ80 ሚሊየን ፓውንድ በላይ የሚጠየቅበት ተጫዋች ሆኗል። በአርሰናል እቅድ ውስጥ ያለው የአስቶንቪላው ተከላካይ ኤዝሪ ኮንሳም በተመሳሳይ ከፍ ያለ ዋጋ ይጠየቅበታል።

የአርሰናል ዝውውር የሚመራው በስፖርቲንግ ዳይሬክተሩ አንድሬ በርታ ነው። አንድሬ በርታ በዋና ስራአስፈፃሚው ሪቻርድ ጋርሊክ እና በክለቡ ምክትል ሊቀመንበር ጆሽ ክሮንኬ እንደሚታገዝ የቴሌግራፉ ሳም ዲን ፅሁፍ ያሳያል።
እነዚህ አካላት ዘንድሮ ያለውን የተጫዋቾች ዋጋ ንረት ተገንዝበው በፍጥነት ካልተንቀሳቀሱ የትችት ናዳውን ለመመከት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። አርሰናል የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ በመሆኑ እና የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ በመድረሱ በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ ያለውን ገቢ አግኝቷል።
የተወሰኑ ደጋፊዎች ጥያቄም ገንዘቡ ካለ እንደሌሎቹ ክለቦች ለምን ጊዜ ሳይፈጅ አያወጣም የሚል ነው። ችግሩ አርሰናል በሚገዛው ልክ በመሸጥ የተዋጣለት ክለብ አይደለም። ባለፈው ዓመት ወደ ክለቡ ለቀላቀላቸው ተጫዋቾች 270 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ አድርጓል። ከሽያጭ ያገኘው ግን 9 ሚሊየን ፓውንድ ብቻ ነው። ክለቡ እንደፈለገ እየገዛ መሸጥ የማይችል ከሆነ ሂሳቡን ማመጣጠን አይችልም።
አርሰናል ነገሮችን ለማስተካከል በቂ ጊዜ አለው። ሊያስፈርማቸው ይችላል ተብለው ስማቸው የሚጠቀሱ ተጫዋቾች ደረጃቸው ከፍ ያሉ ናቸው። ሁሊያን አልቫሬዝ ፣ ቪኒሺየስ ጁኒዮር እና ቡርኖ ጉማይሬሽ በዋናነት ስማቸው ከአርሰናል ጋር እየተነሱ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
ነገር ግን እንደ ቴሌግራፉ ፀሃፊ ሳም ዲን አስተያየት አርሰናል ከፍ ያለ ምኞቱን የሚያሳይ ብልሃት የታከለበትን ዝውውር ለመፈፀም ከዚህ በላይ መዘግየት የለበትም።
በሸዋንግዛው ግርማ
See less