AMN – መጋቢት 7/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሃይማኖቶች በልማትና በሃገረ መንግስት ግንባታ ላይ ያላቸዉን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ በመዲናዋ ከሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤም በመዲናዋ ከሚገኙ የእስልምና እምነት አባቶች ጋር የማጠቃለያ ምክክር ያካሄዱ ሲሆን ተሳታፊዎችም ከለዉጡ ወዲህ እንደ ሃይማኖት ተቋም እና እንደ ሃገር በተገኙ ለዉጦች እና በቀጣይ ሊቀረፉ በሚገባቸዉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ላይ የተለያዩ ሃሳብና አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
ከለዉጡ በፊት የነበሩት አመታት የህዝበ ሙስሊሙ ድምጽ ያልተሰማበት፤ የመስጊድና የቀብር ቦታ ችግር ያልተፈታበት፤ ሃይማኖታዊ በአላትን በተፈለገዉ ሁኔታ ለማክበር ያልተቻለበት እና የስብእና ጥሰት የሚስተዋልበት ወቅት እንደ ነበር አንስተዋል፡፡
ከለዉጡ ወዲህ ግን የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ በሂደት ምላሽ በማግኘት ላይ ይገኛል፤ ያልተመለሱ ጥያቄዎችም በሂደት እንደሚመለሱ ተስፋ አለን ብለዋል፡፡
አዲስ አበባን እንደ ስሟ ዉብ አበባ ለማድረግ በለዉጡ መንግስት ቃል የተገባዉ በተግባር ተፈጽሟል ያሉት ተሳታፊዎቹ የተጀመረዉ ለዉጥ በማንኛዉም ሁኔታ ሳይደናቀፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፤ እኛም የበኩላችንን ደርሻ እንወጣለን ብለዋል፡፡
አርአያነት ያለዉ ተግባር በየትኛዉም አካል ቢፈጸም እዉቅና የመስጠትና የማመስገን ሃላፊነት አለብን ያሉት የእስልምና ሃይማኖት አባቶች፣ ከህዝብ የሚሰበሰበዉ ግብር ሳይባክን ለመዲናዋ ልማት እና ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየዋለ መሆኑን መስክረዋል፡፡

የለዉጡ መንግስት አቅመ ደካማ እና ዝቅተኛ ገቢ ካላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ማዕድ የሚጋራ ነዉ ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን አድንቀዋል፡፡
የኮሪደርና ወንዝ ደርቻ ልማትን ጨምሮ አዲስ አበባን መልሶ ለማልማት በተከናወኑ በርካታ ስራዎች አዲስ አበባ አዲስ ገጽታን ተላብሳለች፤ ለዉጡም በግልጽ የሚታይ ነዉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብት አላት ያሉት ተሳታዎቹ፣ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በህብረት ገንብተን አስመርቀናል፤ የባህር በር ጥያቄም ምላሽ እንዲያገኝ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡
ሙስሊም ማለት ሰላም ነዉ፤ ለዚህም በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ህዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ