የአዲስ አበባ ትራንስፖርት አዲስ መልክ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ትራንስፖርት አዲስ መልክ

AMN – መጋቢት 8/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከጭስ እና ከከባድ የድምፅ ብክለት ተላቃ፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት አማራጮችን ማስተናገድ ጀምራለች።

የከተማዋን የሙቀት መጠን ከሚጨምሩት የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ፊት በማዞር፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የ”ስማርት” ትራንስፖርት ሥርዓት እውን መሆን ጀምሯል።

ለዚህ ስኬት ደግሞ የአዲሶቹ የኮሪደር ልማት መንገዶች መጠናቀቅ እና የኤሌክትሪክ እስኩተሮች አገልግሎት መጀመር አዲስ ተስፋን ይዘው ብቅ ብለዋል።

የከተማዋን የትራንስፖርት ዘርፍ ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች መካከል አንዱ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ እስኩተሮች ናቸው።

ወጣት መርሲሞይ ኃይሉ ይህንን ስማርት ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ግንባር ቀደም ሆኗል።

እነዚህ እስኩተሮች ተራ የመጓጓዣ መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ባህል የሚቀይሩ እና ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው።

እንደ መርሲሞይ ገለጻ፣ እነዚህ እስኩተሮች በአንድ ሙሉ ቻርጅ እንደ መንገዱ ሁኔታ ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላሉ።

“በድሮው የትራንስፖርት ሥርዓት መቀጠል አንችልም፤ ወደ ፊት እያየን ወደ ኋላ መመለስ ይከብዳል” የሚለው መርሲሞይ፣ ይህ ለውጥ ከመጓጓዣነት ባለፈ የሰዎችን አስተሳሰብ ጭምር የሚቀይር መሆኑን ይናገራል።

የእስኩተሮቹ አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ ተጠቃሚዎች የሞባይል መተግበሪያን በመጠቀም በእስኩተሩ ላይ ያለውን የQR ኮድ ስካን በማድረግ ጉዟቸውን መጀመር እንደሚቻል ወጣቱ አብራርቷል።

እስኩተሩን ካሉበት ቦታ አንስተው መድረሻቸው ላይ ሲደርሱ እዚያው ትተውት መሄድ የሚችሉና ክፍያው በደቂቃ የሚታሰብ መሆኑን ገልጿል፡፡

እያንዳንዱ እስኩተር የራሱ GPS ያለው ሲሆን፣ የባትሪ መጠኑ እና ጤንነቱ ከርቀት ቁጥጥር ይደረግበታል።

በአሁኑ ወቅት ከስካይላይት ሆቴል እስከ መስቀል አደባባይ፣ ከቦሌ እስከ መገናኛ እና በፒያሳ አካባቢ ያሉ መንገዶች ለአገልግሎቱ ዝግጁ ሆነዋል።

መርሲሞይ ስለ ኮሪደር ልማቱ ሲናገር “እኔ ስዊድን ነው ያደኩት፤ እዚያ ከማየው የኮሪደር ልማት እኛ ሀገር ያለው በልጦ መገኘቱ በጣም አስገርሞኛል፣ አኩርቶኛልም” ይላል።

ይህ የተመቻቸ መንገድ ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ያምናል።

መንግስት የሙቀት አማቂ ጋዝን ለመቀነስ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ከማበረታታት ባለፈ፣ እንደ እስኩተር እና ብስክሌት ያሉ ለአካባቢ ተስማሚ የትራንስፖርት አማራጮችን በትኩረት እየደገፈ ይገኛል።

በአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአማቂ ጋዝ ቅነሳ እና የአየር ጥራት ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን መለሰ፣ ይህ የአየር ብክለትን ከመቀነሱም በላይ የከተማዋን የኑሮ ጥራት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review