AMN – መጋቢት 10/2018
የኢራን ጦርነት ያሰከተለው የነዳጅ ዋጋ እጥረት እና ንረት ፣ ሃገራት ትኩረታቸውን ወደ ታዳሽ ሃይሎች እንዲያፋጥኑ እያደረገ ይገኛል፡፡ ዋንኛ የነዳጅ መተላለፊያ የሆነዉ የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት በያዝነው አስርት ዓመታት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ዓለም የሃይል አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠማት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ሁነቱ የከርሰ ምድር ነዳጅ ላይ ጥገኛ የመሆን ዘመን ማብቃት አለበት የሚለውን የዓየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች ሀሳብም ምልከታም የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው እያስገደደ ያለ ሁነት ነው። ሮይተርስ እንደዘገበው የሆርሙዝ ወሸመጥ መዘጋቱን ተከትሎ አንድ አራተኛ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ተቋርጧል።
የኢነርጂ አቅርቦት ደህንነት ጉዳይ እንደዚህ ወቅት አሳሳቢ ሆኖም አያውቅም፤ ሀገራትም አማራጮችን ማስፋት ላይ እያማተሩ ይገኛሉ።

የኢነርጂ ባለሙያዎች እንደሚሉት የተወሰኑ ሐገራት ቀደም ብለው ትኩረታቸውን ወደ ታዳሸ ሃይል በማድረጋቸው ከጥቂት አመታት በፊት በመሰል ቀውሶች ይኖራቸው ከነበረው ጫና የተሻለ ሁኔታ ላይ ራሳቸውን ማስቀመጥ ችለዋል።
የታዳሽ ሃይል አጠቃቀም ፥ የባቲሪ ስርዓት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፈጣን እድገት ማሳየታቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት።
ኤን ፒ አር እንዳሰፈረው መረጃ ከሆነ በቻይና ከግማሽ በላይ ለሽያጭ የሚውሉ አዳዲስ መኪኖች በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ናቸው። በኔፓል ደግሞ ከ70 በመቶ ይበልጣል።
የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ እየናረ ቢመጣም እንደ ፓኪስታን ያሉ ሀገራት የፀሐይ ሃይል አቅርቦትን በማሳደጋቸው መቋቋም ችለዋል። ኢምበር የተሰኘ የዳታ ምንጭን ዋቢ አድርጎ ኤን ፒ አር እንደዘገበው እኤአ በ2023 ፥ ፓኪስታን 41 ጊጋ ዋት የፀሐይ ሃይል መቀበያ ሳህኖችን ከቻይና ገዝታለች።

በተወሰኑ የአፍሪካ እና የደቡብ አሜሪካ ሐገራት ዘንድ የትኛው ላይ እናተኩር በሚለው ማመንታት ቢኖርም ፥ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የታዳሽ ሃይላት አማራጮችን ማስፋት ላይ አተኩረዋል።
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የፖሊሲ ርምጃዎችን ተግባራዊ አድርጋለች። የኤሌክትሪክ አቅርቦቷም ከታዳሽ ሃይሎች የሚመነጭ ነው።
ኡራጓይ እኤአ 2008 ካጋጠማት የፋይናንስ ቀውስ ወዲህ ከከርሰ ምድር ሃይል ጥገኝነት በሰራችው ስራ አሁን ላይ 90 በመቶ የሃይል አቅርቦቷን ከታዳሽ ሃይል የሚመነጭ ማድረጓን ዶቸቨሌ ጠቅሷል። የትራንስፖርት ዘርፏንም ወደ ኤሌክትሪክ ለመቀየር እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።
የጋዝና የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ይችላል ፥ ፀሐይ እና ነፋስ ግን በሆርሙዝ ሰርጥ የሚሆነው ነገር ሰቅዞ የሚይዛቸው አይደለም የሚሉት በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የኢነርጂና አየር ንብረት ፕሮፌሰር ጃን ሮሴኖው ፥ ከኤን ፒ አር ጋር ባደረጉት ቆይታ ሐገራት የከርሰ ምድር ነዳጅ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ማላቀቅ በስትራቴጂ ሊተገብሩት የሚገባ መሆኑን መክረዋል።
በታደሰ ሽፈራው