የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ጥቁምታ

You are currently viewing የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ጥቁምታ

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሙዚቃ፣ የስዕል አውደ ርዕይ፣ የመጽሐፍት ምረቃ፣ የግጥም ምሽት እና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት

የ“ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍ 60ኛ ዓመት በዛሬው እለት ይከበራል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ ኤምሬትስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ ታዬ አሰፋ (ዶ/ር)፣ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ እና ደራሲ ህይወት እምሻውን ጨምሮ በርካታ ደራሲያንና ታዳሚያን እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ መጽሐፉ የታተመበትን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ይህ ፕሮግራም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ቀበና ካቶሊክ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ፣ ወደ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት በሚወስደው መንገድ፣ ባማ አዲስ ሕንፃ አጠገብ፣ FSS አዳራሽ ይካሄዳል፡፡

በሌላ መረጃ “ፍቅር አይጻፍም” የተሰኘው መጽሐፍ ከነገ በስትያ ይመረቃል፡፡ የገጣሚ አቤል ያለውን ግጥምና ሽርፍራፊ ታሪኮችን የያዘው ይህ መጽሐፍ 4 ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጽሐፍት አዳራሽ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ይመረቃል፡፡ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይም አንጋፋና ወጣት ደራሲያንና ገጣሚያን እንደሚታደሙ ተገልጿል፡፡

የስዕል አውደ ርዕይ

ሴት ደራሲያን ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት “የፈጠራ ጉዞን ማስተጋባት” የተሰኘው የስዕል አውደ ርዕይ በዕይታ ላይ ይገኛል፡፡ አውደ ርዕዩ ከሴት ሰዓሊያን ማህበር የ17 ሰዓሊያን ስራዎች የቀረበበት ነው፡፡ ፈንድቃ የባህል ማዕከል እና ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በመተባበር ያዘጋጁት ይህ አውደ ርዕይ 24 ሰዓት ለተመልካች ክፍት  ሲሆን የፊታችን መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡

በተጨማሪም የሚኪያስ አበራ የግል የሥዕል ኤግዚቢሽን በአርታዊ ጋለሪ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡ “የመንደር ሹክሹክታ፡ ትዝታ እና ንብረት” (Village Whispers: Memory and Property) የተሰኘ ስያሜ የሰጠው ይህ አውደ ርዕይ  የማህበረሰቡን አኗኗር፣ ታሪክ፣ ህይወት እና ተስፋ የሚያሳዩ ስራዎች የቀረቡበት ነው፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ መጋቢት 27 ቀን 2018 የሚቆይ ሲሆን፤ እየታየ የሚገኘው ደግሞ ቦሌ፣ ብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ስኩል አጠገብ  ኬኬር ሆምስ 2ኛ ፎቅ በሚገኘው አርታዊ ጋለሪ ውስጥ ነው፡፡

የግጥም ምሽት

“ወለሎ Night” የተሰኘ የግጥም ምሽት በነገው እለት ይካሄዳል፡፡ ይህ የግጥምና የጥበብ ምሽት  ነገ ከምሽቱ 11:00 ሰዓት ጀምሮ ቦሌ ቡልቡላ በሚገኘው ሪፌንቲ አፓርትመንት እንደሚካሄድ ተገልጿል። በመርሃ ግብሩ ላይ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ስራቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡

ሙዚቃ

“አራዳ ነው ቤቷ“ የተሰኘ ነጠላ ዜማ ትናንት ምሽት ለአድማጭ ተመልካች ይፋ ሆነ፡፡ ይህ የድምፃዊ ዘርአብሩክ ሰማው የሙዚቃ ስራ በናሆም ሬከርድስ አማካኝት ለህዝብ ደርሷል፡፡ ድምጻዊው ከዚህ ቀደም ለአንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን የግጥምና የዜማ ስራዎችን አበርክቷል፡፡ ከዚህ በፊት ምን ተረፈሽ፣ ገላጋይ እንዳትረሽው የተሰኙ ነጠላ ዜማዎችን ለህዝብ ያደረሰ ሲሆን አሁን ደግሞ ከረጅም ዓመታት በኋላ ይህን ስራ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡  በሙዚቃ ስራው በግጥም ወንደሰን ይሁብ፣ በሙዚቃ ቅንብርና ሚክሲንግ ስማገኘው ሳሙኤል እና በዜማ ራሱ  ዘርአብሩክ ሰማው ተሳትፈውበታል፡፡

​የቴአትር መርሃ-ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ። ቅዳሜ ከ7፡30 ሰዓት ጀምሮ ንጉስ አርማህ፣ 11፡30 ሰዓት ዴጊያ፣ እሁድ በ7፡30 ሰዓት ንጉሥ አርማህ ቴአትር እንዲሁም 11፡30 ሰዓት እምዩ ብረቷ ቴአትሮች በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review