AMN-መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ በአዲስ አበባ የመጀመሪያውን የኢትዮ-ጣሊያን የኮንስትራክሽን፣ የመሰረተ ልማትና የከተማ መልሶ ማልማት ፎረም የእኛ ሚኒስትሮች እና የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርና የዓለምቀፍ ትብብር ሀላፊ በተገኙበት አስጀምረናል ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕከል፣ አሁን ላይ በመዲናችን የንግድ እንቅስቃሴ እያደገ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።
አዲስ አበባ በፍጥነት እየተለወጠች በመሆኗ፣ ይህ የኢትዮ-ጣሊያን የኮንስትራክሽን፣ የመሰረተ ልማትና የከተማ መልሶ ማልማት ፎረም መካሄዱ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና እጅግ አስፈላጊ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለግል ዘርፉና ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ትልቅ ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ከንቲባ አዳነች የጣሊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዚህች በተለወጠች ከተማ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ ሲሉ አሳስበዋል።

ከንቲባ አደነች አክለውም አዲስ አበባ የተለወጠችው በገፅታ ብቻ ሳይሆን ቢዝነስ ለመስራት አመቺና ቀላል በመሆኗም ጭምር ነው። ኢንቨስት ለማድረግ ስትመጡ በፈጣንና ቀልጣፋ አሰራር ለማስተናገድ እንደ ‘መሶብ’ ያሉ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎቶች ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
አስተዳደራችን የግል ዘርፉን ለመደገፍ እጅግ ቁርጠኛ ሲሆን፣ ይህ ፎረም ለዚህ ግብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው እርግጠኞች ነን ሲሉም አስገንዝበዋል።
ክቡራን የፎረሙ ተሳታፊዎች፤ በአዲስ አበባ የሚኖራችሁ ቆይታ ፍሬያማ እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።