AMN- መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
“ቂም ይዞ ጸሎት፣ ሳል ይዞ ስርቆት” እንዲሉ፤ በሰው ተቀይመው፣ በልብዎ ቂም አርግዘው ያውቃሉ? ያንን ቂም ሰብረው ሲታረቁስ የሚሰማውን የህሊና እረፍትስ ምን ፈጠረብዎት ? እንግዲያውስ ከአስር ዓመታት በላይ የዘለቀን ጥል በይቅርታ አጥፍተው፣ ዛሬ የሰላም አምባሳደር የሆኑትን የቀጨኔ እናቶች እና አባቶችን ታሪክ እናጋራችሁ።
መነሻው ጸሎት፣ መድረሻው ዕርቅ
ታሪኩ የሚጀምረው ዓለምን በሞት ጥላ በሸፈነው የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ነው። የቀጨኔ አካባቢ ነዋሪዎች ፈጣሪ ምህረቱን እንዲያወርድ በህብረት መጸለይ ጀመሩ። ሆኖም አንድ ትልቅ ጥያቄ ተነሳ፡ “ልባችን በቂም ተሞልቶ እንዴት ጸሎታችን ይሰማል?”
ይህ ጥያቄ የብዙዎችን የልብ በር አንኳኳ። ጎረቤት ከጎረቤት፣ ወንድም ከእህት፣ ዘመድ ከዘመድ የተጣላ ሁሉ የውስጡን መናገር ጀመረ። ይህንን የታዘቡ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና እናቶች ወገባቸውን ታጥቀው ተነሱ። ቂምን በፍቅር፣ ግጭትን በስምምነት ለመተካት የጀመሩት ጉዞ ዛሬ ከ600 በላይ ሰዎችን ማስታረቅ ወደቻለ ታላቅ ማህበር አደገ።
የወይዘሮ አሰገደች ዳምጠው እና የአቶ እስጢፋኖስ በለጠ ታሪክ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው። “እንኳን ሰው ከሰው እግር ከእግር ይጋጫል” እንደሚባለው፤ በትንሽ ነገር የተጀመረው ቅሬታቸው ለአስር አመታት ወደ ዘለቀ ጽኑ ጥል ተቀየረ።
እኒህ የዘመናት ጎረቤታሞች ሀዘን ቢደርስ አይጠያየቁም፤ ደስታና ሰርግ ቢኖር አይገባበዙም፤ ዝክርና ማህበር ቢኖር “እሱ/እሷ ካለችበት አልገኝም” ተባባሉ። በዚህ መልክ አመታተ ነጉደዋል ።
ጎረቤት ሆነው እንደ ባዕድ የኖሩባቸው እነዚያ አመታት አልባት ያገኘው በእነዚህ አስታራቂዎች ጥረት ነበር። ዛሬ ወይዘሮ አሰገደችና አቶ እስጢፋኖስ “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” የሚለውን ብሂል በተግባር እየኖሩት ነው።

የሚያስደንቀው ግን የታረቁት ታራቂዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ዛሬ ራሳቸው አስታራቂ ሆነው “ምድረ ገነት ኢትዮጵያ አስታራቂ እናቶች እና አባቶች ማህበርን” ተቀላቅለዋል።
ይህ ማህበር ሰዎችን አስታርቆ “በቃችሁ” አይልም። ይልቁንም፡ የእርቁን መፅናት በቅርበት ይከታተላሉ። ቂም ዳግም እንዳያገረሽ የፍቅር ግንኙነቱን ያጠናክራሉ።
የቤተሰብ ሰላም የሀገር ሰላም መሆኑን በተግባር ያስተምራሉ
“መጣላት በሰውኛ ባህሪ ሊያጋጥም ይችላል፤ ይቅርታ ግን መለኮታዊና የህሊና እረፍት ሰጪ ነው።” — የማህበሩ አባላት መልዕክት ነው ።
የእርስዎ ተራ ነው!
የቀጨኔ እናቶች እና አባቶች ያሳዩን ትልቅ እውነት አለ፡ ሰላም የሚጀምረው ከቤት እና ከጎረቤት ነው። የቤተሰብ ሰላም ከጠፋ የሀገር ሰላም ህልም ይሆናል።
እስኪ ንገሩን? በእናንተ አካባቢ ግጭቶች ሲነሱ የምትፈቱበት ልምድ ምንድነው? እንደ ቀጨኔ እናቶች “ይቅርታ” ለሀገር መድኃኒት ይሆናል ብለው ያምናሉ?
ሀሳባችሁን በኮሜንት አጋሩን!
በቤተልሔም አየነው