በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሙዚቃ፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የመጻሕፍት ምረቃ፣ የግጥም ምሽት እና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጻሕፍት
የ“ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍ 60ኛ ዓመት በዛሬው ዕለት ይከበራል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ ኢሜሪተስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ ታዬ አሰፋ (ዶ/ር)፣ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ እና ደራሲ ሕይወት እምሻውን ጨምሮ በርካታ ደራሲያንና ታዳሚያን እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ መጽሐፉ የታተመበትን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ይህ ፕሮግራም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ቀበና ካቶሊክ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ፣ ወደ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት በሚወስደው መንገድ፣ ባማ አዲስ ሕንፃ አጠገብ፣ FSS አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
በሌላ መረጃ “ፍቅር አይጻፍም” የተሰኘው መጽሐፍ ከነገ በስትያ ይመረቃል፡፡ የገጣሚ አቤል ያለውን ግጥምና ሽርፍራፊ ታሪኮችን የያዘው ይህ መጽሐፍ 4 ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጻሕፍት አዳራሽ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ይመረቃል፡፡ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይም አንጋፋና ወጣት ደራሲያንና ገጣሚያን እንደሚታደሙ ተገልጿል፡፡
የሥዕል አውደ ርዕይ
ሴት ደራሲያን ሥራዎቻቸውን ያቀረቡበት “የፈጠራ ጉዞን ማስተጋባት” የተሰኘው የሥዕል አውደ ርዕይ በዕይታ ላይ ይገኛል፡፡ አውደ ርዕዩ ከሴት ሰዓሊያን ማኅበር የ17 ሰዓሊያን ሥራዎች የቀረበበት ነው፡፡ ፈንድቃ የባህል ማዕከል እና ኃያት ሪጀንሲ ሆቴል በመተባበር ያዘጋጁት ይህ አውደ ርዕይ 24 ሰዓት ለተመልካች ክፍት ሲሆን፣ የፊታችን መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡
በተጨማሪም የሚኪያስ አበራ የግል የሥዕል ኤግዚቢሽን በአርታዊ ጋለሪ በዕይታ ላይ ይገኛል፡፡ “የመንደር ሹክሹክታ፡ ትዝታ እና ንብረት” (Village Whispers: Memory and Property) የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ይህ አውደ ርዕይ የማኅበረሰቡን አኗኗር፣ ታሪክ፣ ሕይወት እና ተስፋ የሚያሳዩ ሥራዎች የቀረቡበት ነው፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ እየታየ የሚገኘው ደግሞ ቦሌ፣ ብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ስኩል አጠገብ ኬኬር ሆምስ 2ኛ ፎቅ በሚገኘው አርታዊ ጋለሪ ውስጥ ነው፡፡
የግጥም ምሽት
“ወለሎ Night” የተሰኘ የግጥም ምሽት በነገው ዕለት ይካሄዳል። ይህ የግጥምና የጥበብ ምሽት ነገ ከምሽቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ቦሌ ቡልቡላ በሚገኘው ሪፌንቲ አፓርትመንት እንደሚካሄድ ተገልጿል። በመርሃ ግብሩ ላይ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ሥራቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።
ሙዚቃ
“አራዳ ነው ቤቷ“ የተሰኘ ነጠላ ዜማ ትናንት ምሽት ለአድማጭ ተመልካች ይፋ ሆነ፡፡ ይህ የድምፃዊ ዘርአብሩክ ሰማው የሙዚቃ ሥራ በናሆም ሬከርድስ አማካኝነት ለሕዝብ ደርሷል። ድምጻዊው ከዚህ ቀደም ለአንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን የግጥምና የዜማ ሥራዎችን አበርክቷል። ከዚህ በፊት “ምን ተረፈሽ” እና “ገላጋይ እንዳትረሽው” የተሰኙ ነጠላ ዜማዎችን ለሕዝብ ያደረሰ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከረጅም ዓመታት በኋላ ይህን ሥራ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በሙዚቃ ሥራው በግጥም ወንደሰን ይሁብ፣ በሙዚቃ ቅንብርና ሚክሲንግ ስማገኘው ሳሙኤል እና በዜማ ራሱ ዘርአብሩክ ሰማው ተሳትፈውበታል፡፡
የቴአትር መርሃ ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ። ቅዳሜ ከ7፡30 ሰዓት ጀምሮ “ንጉሥ አርማህ”፣ 11፡30 ሰዓት “ዴጊያ”፤ እሁድ በ7፡30 ሰዓት “ንጉሥ አርማህ” ቴአትር እንዲሁም 11፡30 ሰዓት “እምዬ ብረቷ” ቴአትሮች በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ፡፡
በጊዜው አማረ