ጥበብና ጥበበኞችን ያገናኙ ስፍራዎች

You are currently viewing ጥበብና ጥበበኞችን ያገናኙ ስፍራዎች

አዲስ አበባ በታሪካዊ ጠቀሜታዋ፣ በባህል ሀብቷና በዓለም የፖለቲካ ማዕከልነቷ የምትታወቅ  ከተማ ናት። ሆኖም ለረጅም አመታት የከተማዋ ነዋሪዎችና እንግዶች የሚዝናኑባቸው፣ ጥበባዊ ስራዎች የሚቀርቡባቸውና ንጹህ አየር የሚያገኙባቸው ክፍት የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች እጥረት በጉልህ ይታይባት ነበር።

የከተማዋ የህዝብ ብዛት በፍጥነት እያደገ መምጣቱ፣ ክፍት ቦታዎች ሁሉ ለግንባታ መዋላቸው  በአካባቢ ጥበቃና በማህበራዊ መዝናኛ ጉዳይ ትልቅ ስጋት ሆኖ ነበር። ይህም ወጣቶችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የፈጠራ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡባቸው የአንፊ-ቴአትርና የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች እጥረት እንዲስተዋል አድርጎ ቆይቷል።

አሁን ላይ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ገጽታዋን ሙሉ በሙሉ ቀይረውታል። ቀደም ሲል ለቆሻሻ መጣያነት ይውሉ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ዛሬ ወደ ውብ መናፈሻዎችና ለእግር ጉዞ ምቹ ወደ ሆኑ መንገዶች ተቀይረዋል። ይህም ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለዓይን ማራኪና ለኑሮ ተስማሚ በማድረግ ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

በእነዚህ የልማት ስራዎች ውስጥ ጎልተው የሚታዩት አዳዲስ ፓርኮች፣ ፕላዛዎችና ዘመናዊ የአንፊ-ቴአትሮች የከተማዋን የኪነ ጥበብ ህይወት አድሰውታል። የዘርፉ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን በነጻነትና በክፍት አየር የሚያቀርቡባቸው መድረኮች በመፈጠራቸው፣ ከተማዋ የባህልና የጥበብ መንደር እንድትሆን አቅም የፈጠሩ ናቸው። ይህም ነዋሪው ጥበብን ከአረንጓዴ ልማት ጋር አጣምሮ እንዲያገኝና ማህበራዊ ትስስሩን እንዲያጠናክር ትልቅ እድል ፈጥሯል ይላል፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያው ቢተው ዳዊት።

ቢተው ከጓደኞቹ ጋር በመሆን አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ጋር ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የኪነት ማህበር ቢመሰርቱም፣ ቀጣዩ ጉዟቸው ግን በመድረክ እጥረት የታጠረ ነበር። ይህ መሰረታዊ ችግር የጥበብ ስራዎች ለህዝብ እንዳይደርሱና የፈጠራ አቅም እንዲገታ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።

በወቅቱ የነበረው አማራጭ በየወረዳው በሚገኙና የወጣቶች የሰብዕና መገንቢያ ማዕከል ጠባብ ስፍራዎች እና አዳራሾች ብቻ ነበሩ። ቢተው ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገረው፣ እነዚህ ቦታዎች ለልምምድም ሆነ ለዝግጅት ማቅረቢያ እጅግ የተጨናነቁና የማይመቹ ነበሩ። በጠባብ ክፍሎች ውስጥ ተጠጋግቶ መስራትና የድምፅና የብርሃን ቴክኖሎጂ እጥረት የጥበብ ስራዎቹን ጥራት የሚቀንስ ከመሆኑም ባለፈ፣ ባለሙያዎቹ የፈጠራ አቅማቸውን በነጻነት እንዳያወጡ አድርጓቸው ቆይቷል።

ከቦታው ጥበት በተጨማሪ፣ የማዕከላቱ ለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችና ለስብሰባዎች ክፍት መሆን ለዘርፉ ባለሙያዎች ሌላው ፈታኝ ሁኔታ ነበር። አንድ የኪነ ጥበብ ቡድን ለሳምንታት የለፋበትን ዝግጅት ለማቅረብ ሲዘጋጅ፣ ቦታው ለድንገተኛ ስብሰባ ወይም ለሌላ የመንግስት ጉዳይ ስለሚፈለግ ዝግጅቱ እንዲሰረዝ ወይም እንዲራዘም ይገደድ ነበር። ይህ በባለሙያዎቹ ስነ-ልቦና ላይ ተስፋ መቁረጥን ይፈጥር፣ ጥበብን እንደ ሙያ አድርገው ለሚሰሩ ወጣቶች ደግሞ መንገዱን አዳጋች ሲያደርግባቸው ቆይቷል።

ዛሬ ግን በአዲስ አበባ ከተማ የታየው ለውጥ ይህንን ታሪክ ሙሉ በሙሉ የቀየረና አዲስ ተስፋ የሰነቀ ሆኗል። ከተማዋ አሁን የውብ ፓርኮች፣ የሰፊ ፕላዛዎችና ዘመናዊ የአንፊ-ቴአትሮች መገኛ ሆናለች። እነዚህ ቦታዎች መዝናኛ ብቻ ሳይሆኑ፣ እንደ ቢተው ያሉ የኪነት ባለሙያዎች በነጻነትና በኩራት ስራዎቻቸውን ለታዳሚ የሚያቀርቡባቸው ድንቅ መድረኮች ናቸው። ዛሬ ላይ ባለሙያዎች መድረክ ፍለጋ መንከራተታቸው ቀርቶ፣ የፈጠራ ስራቸውን ለማቅረብ የሚያስችል ስፍራ ማግኘት ችለዋል።

አዳዲሶቹ የመዝናኛና የጥበብ ስፍራዎች ራሳቸው “ጥበብ” ሆነው መገንባታቸው ለከተማዋ ልዩ ድምቀት ሰጥቷታል ይላል። ሰዎች በእነዚህ ውብ ቦታዎች ፎቶ እየተነሱና እየተዝናኑ ጥበብን በአካል የሚታደሙበት እድል ተፈጥሯል። አካባቢው ካለው ተፈጥሯዊ ውበትና ዘመናዊ ግንባታ ጋር ተዳምሮ፣ የኪነ ጥበብ ስራዎች ከበፊቱ በበለጠ ማራኪና ለዓይን የሚስቡ ሆነዋል። ይህ ሁነት ከሰሞኑም በአራዳ ፓርክ ተንጸባርቋል፡፡

የአዲስ አበባ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በአራዳ ፖርክ በርካታ የመዲናዋ ወጣቶች የተሳተፉበት የኪነ ጥበብ እና የስፖርት ፌስቲቫል ባካሄደበት ወቅት በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ ፓርኮች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ወጣቶች የፈጠራ ስራዎቻቸውን በነፃነት የሚያሳዩባቸው የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች መሆናቸው ታይቷል፡፡ ይህም ወጣቶች ተሰጥኦአቸውን እንዲያሳድጉና በዘርፉ ያላቸውን ተወዳዳሪነት እንዲያጠናክሩ ዕድል ሰጥቷል።

ይህ መድረክ ወጣቶች በስፖርት፣ ሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በግጥምና በስነ-ስዕል ዘርፎች ያላቸውን ተሰጥኦ ለታዳሚው እንዲያሳዩ ሰፊ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጥበብ ፍሬዎችን በአንድ ማዕከል ያገናኘ ልዩ ክስተትም ሆኗል።

በፌስቲቫሉ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሰጡት አስተያየት፤ በመዲናዋ በኮሪደር ልማት የተገነቡ ዘመናዊ የመዝናኛ ስፍራዎች ተሰጥኦቸውን በነፃነት እንዲያጎለብቱና ለህዝብ እንዲያቀርቡ ትልቅ እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑንና እንደነዚህ አይነት መድረኮች ቶሎ ቶሎ ቢዘጋጁ ፍላጎታቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በመድረኩ ስራዋን ለታዳሚያን ያቀረበችው ወጣት መቅደስ ፋሲካው፣ “ቦታዎቹ የድምጽ ጥናት ለማድረግና ለማቅረብ ምቹ  ናቸው፡፡ እነዚህ ቦታዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎችም መስፋፋት አለባቸው” ስትል ሃሳቧን ገልጻለች፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ የዘመናዊ-ባህል ቡድን ተጠሪ የሆነው ወጣት ሙዚቀኛ  ዘላለም እሸቱ  ለአዲስ ልሳን እንደገለጸው፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የተገነቡት አዳዲስ ፓርኮችና አንፊ ቴአትሮች ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ ዕድል ፈጥረዋል። በተለይም በአራት ኪሎ ፕላዛና በተለያዩ መሰል ስፍራዎች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ለታዳሚ ማቅረብ መቻላቸው ቦታዎቹ ባላቸው ንፅህናና ማራኪ ውበት ምክንያት ለጥበብ ሥራዎች እጅግ ምቹ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ አድርጓል። እነዚህ ስፍራዎች በዘመናዊ መልኩ መገንባታቸው የከተማዋን ድምቀት ከመጨመሩም ባለፈ፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከሕዝብ ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ አዲስ መድረክ ሆኗቸዋል።

ሙዚቀኛው አክሎም፣ የተገኘው ዕድል መልካም ቢሆንም የኪነ-ጥበብ ቡድኖች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉ አመልክቷል። በተለይም የወጣቶቹን የመስራት አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የተደራጁ የልምምድ ቦታዎች ቢመቻቹ፣ የፋይናንስ ድጋፍ ቢደረግና የባህል አልባሳት አቅርቦት ችግሮች ቢፈቱ የኪነ-ጥበብ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚቻልና እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከተሟሉ፣ ወጣቶቹ ካላቸው ከፍተኛ የፈጠራ አቅምና አሁን ካለው የመዲናዋ ለኪነ ጥበብ ምቹነት አንፃር  ተወዳዳሪ ሥራዎችን ለማቀረብ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ምቹ፣ ውብና ጽዱ እየሆነች ነው፡፡  በመዲናችን ለሁሉም ማህበረሰብ የመዝናኛ ቦታዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ወደፊትም በእነዚህ ቦታዎች ላይ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን እያዘጋጀን ወጣቶች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና እንዲዝናኑ ለማድረግ በኮሪደር ልማቱ በተሰሩ የመዝናኛ ስፍራዎች መርሃ ግብሮች እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የፓርኮችና የአንፊ-ቴአትሮች ግንባታ  ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ አዲስ ህይወት ሰጥተውታል። ቢተው እንደሚለው፣ ከሰሞኑ አራዳ ፓርክና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬም ያየሁት ከተማዋ ለነዋሪዎቿ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ የምትመችና የጥበብ ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ነው። እንዲህ ያሉ የኪነ-ጥበብ መድረኮች ተጠናክረው መቀጠላቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የጥበብ ባለሙያዎችን ለማፍራትና የአዲስ አበባን ብሩህ ገጽታ ለዓለም ለማሳየት ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል።

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review