AMN መጋቢት 24/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ በታሪካዊቷ ቀን በመጋቢት 24 ዕለት ለከተማችን በጉለሌ ክፍለ ከተማ 6ተኛውን‘ አዲስ መሶብ ዲጂታል አንድ ማእከል ‘የመንግሥት አገልግሎትን ስራ አስጀምረናል ብለዋል፡፡
መጋቢት 24 ኢትዮዽያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሻገር ቃል ኪዳን የተገባበት ታሪካዊ ቀን ነው። አገራዊ ለውጡ የመጣው ለሁሉም፣ ከሁሉምና በሁሉም ነው። ከለውጡ ወዲህ የሚታዩና ተጨባጭ የሆኑ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡት በጋራ ጥረታችን ነው። ይህ ለውጥ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ስብራቶቻችን እንዲጠገኑና ወደ ከፍታ እንድንጓዝ እጅግ ጠንካራ መሰረት የጣለ ነው ብለዋል፡፡
“እንሰራለን፤ እንችላለን!” ብለን በጋራ በተነሳንባቸው ዓመታት፣ ከኋላ ቀር የፖለቲካ ባህሎች ተላቀን ችግሮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ሂደት ላይ ገብተናል። ስምንት ዓመታት፤ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሽግግር ወደ ዘመናዊ እና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገብን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የተሰበሩ ማህበራዊ እሴቶችን በማከም ማህበራዊ ፍትህ እንዲነግስ የሚስችሉ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በተለይም በከተማችን የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖችን በተለይም የሀገር ባለውለታዎችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችንና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች ከአስቸጋሪ ኑሮ አውጥተን የሰውን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲኖሩ አድርገናል።
ባዶ ምሳ ዕቃ ይዘው ወደ ትምህርት ገበታ ይመጡ የነበሩ ሕፃናትን እኩል በልተውና ለብሰው እንዲማሩ ከማድረግ ባለፈ፣ አዲስ አበባን ሕፃናትን ለማሳደግ ተመራጭ ከተማ አድርገናታል።
ሌላው ስኬት የመንግስት የተቋማት ስብራትን በመጠገን ነፃ፣ ገለልተኛ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ ጠንካራ ተቋማት የመገንባት ሽግግር ነው።

ለዘመናት የአገልግሎት ዘርፉን ለመለወጥ ሳይቻል ስር በሰደደ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተተብትቦ የኖረ ቢሆንም የለውጡ መንግስት ቃል በገባው መሰረት ችግሩን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የሚለውጥ ‘የመሶብ’ ዲጂታል አንድ ማዕከልን በመተግበር ለተገልጋዩ እፎይታን ይዞ መጥቷል ብለዋል፡፡
የነዚህ የለወጥ ፍሬዎች ዋንኛ ተጠቃሚ የሆነው የአዲስ አበባ ህዝብም ማልዶ ወደ አደባባዮች በመውጣት የዘወትር ድጋፋን እንደገና አጽንቷል።
ጅማሬያችን ትላንት ቢሆንም ከህዝባችን ጋር ያሳካነው ድል እና የደረስንበት ርቀት ቀላል አይደለም።
የኢትዮዸያን ብልፅግና ሊያስቀረው የሚችል አንዳችም ምድራዊ ሀይል የለም ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡