AMN — ሚያዝያ 21 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ባለፉት አምስት ዓመታት ያስመዘገበቻቸው ሁለንተናዊ የልማት ስኬቶች እና እያስተናገደቻቸው የሚገኙ ዓለም አቀፍ የስፖርት ኩነቶች፣ ኢትዮጵያ ቀጣዩን ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ አቅም እንደፈጠረ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት አመት የ9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ እንደገለጹት አዲስ አበባ በስፓርት ልማት አመርቂ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡
በከተማዋ በስኬት የተካሄዱት የግራንድ ፕሪ ሩጫ፣ የቦክስ እና የሳይክል ውድድሮች አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የስፖርት መዳረሻ እያደረጓት መሆኑን ነዉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተናገሩት፡፡

የመዲናዋ ነዋሪ ለስፖርት ያለው ከፍተኛ ፍቅር፣ ኢትዮጵያ የ2027 ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናን እንድታስተናግድ ለሚቀርበው ጥያቄ እንደ ትልቅ ግብዓት የሚያገለግል መሆኑንም ከንቲባዋ አመልክተዋል።
መዲናዋ ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ወደ ትልቅ ምዕራፍ መሻገሯን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ በተለይም የአረንጓዴ ልማት ሽፋኑ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 22 በመቶ ከፍ ማለቱንና በቀጣይ ዓመት ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ግብ መቀመጡን ይፋ አድርገዋል።
ይህም መዲናዋን ስፓርትን ጨምሮ ለተለያዩ አህጉር እና አለም አቀፍ ኩነቶች ምቹ እንድትሆን አስችሏል፡፡
በወርቅነህ አብዮ