AMN-መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “አውደ-ሰላም” የተሰኘው ግዙፍ የህዝብ ውይይት የቴሌቪዥን ፕሮግራም በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።
“ምርጫና ሰላም” በሚል ርዕስ እየተካሄደ ባለው በዚህ የመክፈቻ መርሃ-ግብር ላይ፣ ከ200 በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተገኝተው ከአመራሮችና ከምሁራን ጋር ፊት-ለፊት በመምከር ላይ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በመድረኩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የአውደ-ሰላም የቴሌቪዥን ፕሮግራም የአዲስ አበባ ከተማን ሰላማዊነት ለዓለም የሚያሳይ እና በሰላም ግንባታው ሂደት ውስጥ የህብረተሰቡን የባለቤትነት ተሳትፎ የሚያሰርፅ ነው ብለዋል።

በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (AMN) ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋን ጨምሮ ከፍተኛ የከተማዋ አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ ምሁራን በጥናት የተደገፈ የመወያያ ፅሁፍ አቅርበዋል።
ፕሮግራሙ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት በተለያዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በየወሩ የሚካሄድ ሲሆን፤ ህዝብና ምሁራን የመፍትሄ ሃሳብ የሚያፈልቁበትና ህዝቡ ለአመራሮች ቀጥተኛ ጥያቄና አስተያየት የሚያቀርብበት ዴሞክራሲያዊ አውድ መሆኑ ተገልጿል።
በተመስገን ይመር