የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በማዘመን በአፍሪካ ጽዱ ከሚባሉ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው – አዲስ አበባ

You are currently viewing የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በማዘመን በአፍሪካ ጽዱ ከሚባሉ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው – አዲስ አበባ

AMN ሚያዝያ 5/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ከአሁን ቀደም የነበረው የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እጅግ ኋላ ቀር ከመሆኑም በላይ በመዲናዋ አጠቃላይ ገጽታ ላይ ትልቅ ጠባሳን ያሳደረ ነበር፡፡

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችዉ አዲስ አበባ ከጽዳት ችግር እና መሰል ተገቢ ካልሆኑ ውስንነቶች ጋር በተያያዘ ለበርካታ ትችቶችና ወቀሳዎች ስትዳረግ መቆየቷን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ የጽዳት ጉድለት ዋንኛ የኅብረቱ መነጋገሪ አጀንዳ እስከመሆን ደርሷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ከቆሻሻ ጋር መኖር እርግማን እስኪመስል ድረስ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ምክንያት ለተለያዩ የጤናና ማህበራዊ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡

ከተማን ማደስ ዋንኛ የልማት አካል መሆኑን የተረዳው የለውጡ መንግስት ከቅርብ አመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ በአፍሪካ ደረጃ እውቅናን እንድታገኝ አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመዲናዋን አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ አስመልክቶ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ገለጻ ከተሞች መታደስ አለባቸው በሚል መርህ ልማቱን ስንጀምር በበርካቶች ዘንድ በቂ ግንዛቤ ካለመኖሩም በላይ ተገቢነት የሌላቸው አስተያየቶች ሲሰጡ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከቆሻሻ ጋር መኖር እጣ ፈንታችን አይደለም፤ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ በሥርዓቱ መወገድ አለበት በሚል ጽኑ አቋም ባለፉት የለውጥ አመታት በተሰሩ በርካታ ስራዎች በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያገኘ ለውጥ ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል፡፡

በተሰራው ስራ አዲስ አበባ በአፍሪካ ጽዱ ከሚባሉ 10 ከተሞች መካከል አንዷ ለመሆን በቅታለች ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማን የማደስ ስራው ከመጀመሩ በፊት አዲስ አበባ እስከ 50 ባሉት ደረጃ ውስጥ እንኳን መካተት እንዳልቻለች አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ በፊት በመዲናዋ አንድ የፍሳሽ ማጣሪያ ብቻ ነበር ፤ አሁን ላይ 43 የፍሳሽ ማጣሪያ ማዕከላት ተገንብተዋል፡፡

የቦሌ አራብሳ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያም የመዲናዋን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ይበልጥ ከሚያዘምኑ ፕሮጀክቶች መካከል ዋንኛው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመዲናዋን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ለማዘመን ባለፉት የለውጥ አመታት በተተገበሩ በርካታ ስራዎች አዲስ አበባ ከ250 ከተሞች ጋር ተወዳድራ ማሸነፏንም ገልጸዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review