በበዓላት የአመጋገብ ስርዓታችን ምን መምሰል አለበት?

You are currently viewing በበዓላት የአመጋገብ ስርዓታችን ምን መምሰል አለበት?

AMN-ሚያዝያ 06/2018 ዓ.ም

በበዓላት ወቅት በተለይም ከረጅም የጾም ጊዜ በኋላ የሚዘጋጁ የቅባት ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች በጤናችን ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።

በራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል የስርዓተ ምግብ ስፔሻሊስት የሆኑት አቶ ሱለይማን ፍቅሬ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከበዓል ጋር ተያይዞ በአመጋገብ ለውጥ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችንና መፍትሄዎቻቸውን አብራርተዋል።

በጾም ወቅት የምንወስዳቸው የምግብ አይነቶች የቅባት ይዘታቸው ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ጨጓራችን ምግብ ለመፍጨት የሚጠቀማቸው ኢንዛይሞች ወይም ንጥረ ነገሮች መጠን ይቀንሳል።

ከጾም መልስ ወዲያውኑ ከፍተኛ ቅባት ያላቸውን ምግቦች መውሰድ ደግሞ ጨጓራ ከአዲሱ የአመጋገብ ሁኔታ ጋር ለመላመድ እንዲቸገር ያደርገዋል።

ከፍተኛ ቅባት ያላቸውን የምግብ አይነቶችን በብዛት በምንወስድበት ጊዜ የሆድ መነፋት፣ ደረት እና ጀርባ የማቃጠል ስሜት፣ የሆድ ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና ተጓዳኝ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ሰዎች ብዙ ጊዜ አልኮል መጠጣት “የምግብ መፈጨትን ያፋጥናል” ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑን ባለሙያው አስገንዝበዋል።

ከፍተኛ የአልኮል አጠቃቀም ለተለያዩ የጤና ችግሮች ከመዳረጉ ባለፈ፣ በጉበትና በኩላሊት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል አመጣጥኖ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

በበዓል ወቅት የአመጋገብ ስርዓታቸውን በጥንቃቄ ሊከታተሉ የሚገቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የስኳር ታካሚዎች ዋነኞቹ ናቸው ያሉት አቶ ሱለይማን ቅባት የበዛባቸው ምግቦች፣ ከፍተኛ አልኮል መጠጥ፣ ቅመም እና ጣፋጭ ነገሮችን ከመውሰድ መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

እንዲሁም የደም ግፊትና የኩላሊት ታካሚዎች ከፍ ያለ ጥንቃቄ ማድረግና የጨውና የቅባት መጠንን መቆጣጠር ይገባቸዋል ብለዋል።

እርጉዝ ሴቶችና ጡት የሚያጠቡ እናቶችም ለራሳቸውና ለልጃቸው ጤንነት ሲሉ ከባድና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች መቀነስ እንዳለባቸው መክረዋል።

በዓልን በደስታና በጤና ለማሳለፍ፣ ሰውነታችን ከአዲሱ የአመጋገብ ስርዓት ጋር ቀስ በቀስ እንዲላመድ በማድረግ ጤናችንን እንጠብቅ።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review