የመገናኛ ብዙሃን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወኑ ነው

You are currently viewing የመገናኛ ብዙሃን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወኑ ነው

AMN- ሚያዝያ 7/2018 ዓ.ም

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጩ ህዝብ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መወሰን ይችል ዘንድ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማጎልበት የሚያስችሉ መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎችና የሚዲያ አውታሮች እያቀረቡ መሆናቸውን የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተናገሩ።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን በነጻነት የሚያስተዋውቁበትን አውድ ስለመፍጠራቸውም የሚዲያ ተቋማቱ ተናግረዋል።

ምርጫ የአንድ ሐገር መጻኢ እጣ ፈንታን የሚወስን ትልቅ ሐገራዊ ሁነት ነው ያሉት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቴሌቪዥን ዘርፍ ምልትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ካሳ፣ ሒደቱ ስኬታማ ይሆን ዘንድም የመገናኛ ብዙሐን ተቋማት መሪ ተዋናይ መሆን አለባቸው ብለዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ሐገራዊ ምርጫ ስኬታማ ይሆን ዘንድ እንደ ተቋም በቂ ዝግጅት በማድረግ አስቀድሞ ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ በተለይም ህዝቡ በእውቀት ተመስርቶ የራሱን እድል ይወስን ዘንድ በሁሉም የተቋሙ የመገናኛ አውታሮች የማስተማር ስራ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ምርጫ ሐገር በሌላው ዓለም ያላትን ገጽታ የሚያንጸባርቅ፣ የሁለንተናዊ እድገት መሰረት ነው ያሉት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዜና ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ በበኩላቸው፣ በተለይም ወጣቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ መጻኢ እጣ ፈንታቸውን መወሰን፣ ስለ ምርጫ ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት የሶሻል ሚዲያን በመጠቀም በምቹ አቀራረብ የማስተማር ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ስለ የምርጫ ሐገራዊ ጠቀሜታ የሚረዳበትን ፕሮግራምን በመቅረጽ ተቋሙ ባሉት አስሩም ቻናሎች የመራጮች ትምህርት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን የክልል ማእከል ዲቪዥን ስራ አስፈጻሚ አቶ ገናናው ለገሰ ናቸው።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሳካ ይሆን ዘንድ ከመራጮች ትምህርት ባሻገር ፍትሀዊ የአየር ሰአት በመመደብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ይዘው የመጡትን አጀንዳ በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ እንዲያደርጉ እየሰሩ መሆኑንም ተቋማቱ አንስተዋል።

የምርጫ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎችን በተናጥል ከመዋጋት ባሸገር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙም አመራሮቹ ተናግረዋል።

በሔኖክ ዘነበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review