ካናዳ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች

You are currently viewing ካናዳ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች

AMN – ሚያዝያ 7/2018 ዓ/ም

ካናዳ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የካናዳ አንባሳደር ኒኮላስ ሲማርድ አስታወቁ፡፡

ስድስት አስር ዓመታን ያስቆጠረው የኢትዮ ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በስርዓታዊ ለውጦች ሳይበገር ወደ ጠንካራ የትብብርና አጋርነት ተቀይሯል፡፡

በሁለቱ ሀገራት የስልሳ ዓመታ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞን የዳሰሰና ወደፊት ስለሚኖራቸው ትብብር ላይ የመከረ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ኒኮላስ ሲማርድ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ታሪካዊና ብሄራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በታሪካዊው እና ስድስት አስር ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮ ካናዳ ግንኙነት በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ፣ በሰላምና ፀጥታ ዘርፎች አያሌ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በነደፈቻቸው የጤና እና የትምህርት መሰረተ ልማት ዘርፎች በጋራ በመስራት ትብብራቸውንና አጋርነታቸውን ያረጋገጡ መሆናቸውን ያነሱት አምባሳደሩ ፤ ይህን ጠንካራ ግንኙነት በማስቀጠል በኢንቨስትመትና በዲጂታል ልማት ዘርፍ ወደፊትም በስፋት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰሜን አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አፈወርቅ በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ረዥም ርቀትን የተጓዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር በቀጠናው ሰላም ማስከበር ሂደት ላይ ስኬታማ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተገበረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ያነቃቃ ሲሆን በዚህም ዘርፍ የካናዳ መንግስት ጋር ወደፊት በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በማዕድን ልማት ዘርፍና በሰው ሰራሽ አስተውሎት አብሮ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለትም አመላክተዋል፡፡

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review