እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ አምስት ተጨማሪ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ይጀመራሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ አምስት ተጨማሪ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ይጀመራሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ አምስት ተጨማሪ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ሥራ እንደሚጀምሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት በተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንግግራቸው፤ ቢሮክራሲን ማሻሻልና አሠራርን ማቅለል ጊዜ የሚወስድና ፈታኝ ሥራ እንደነበር አስታውሰው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለኢትዮጵያ ትልቅ የምሥራች ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በቦሌ፣ በልደታ፣ በአዲስ ከተማ፣ በጉለሌ እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች አገልግሎቱ በስፋት እየተሰጠ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት ከ150 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል ሥርዓት መግባታቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ በዚህም ከ150 ሺህ በላይ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል።

አገልግሎቱ አሁን ላይ በሌሎች የሀገሪቱ ከተማ አስተዳደሮችና በክልሎችም ጭምር እየተስፋፋ መሆኑንና አመርቂ እድገት እያሳየ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ የሚመጣ ማንኛውም ተገልጋይ በማዕከላቱ በፍጥነትና በጥራት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።

በቀጣይም ሁሉንም የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል ሥርዓት ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመጥቀስ፤ አገልግሎቱ ባልተጀመረባቸው የቀሩት ክፍለ ከተሞች ላይም እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ አምስት ተጨማሪ ማዕከላትን በመክፈት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review