AMN – ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያን ጨምሮ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ቱባ ባህልና ውብ ተፈጥሮ የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ተከፈተ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ከሮማንያ ሪፐብሊክ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ አዘጋጅቷል።

በአዲስ አበባ ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል የተዘጋጀው አውደ ርዕይ “አፍሪካ በዲፕሎማት ዕይታ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬን ጨምሮ እስከ ግንቦት 17 ፣ 2018ዓ.ም እንደሚቆይ ነው የተገለጸው።
አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ቱባ ባህል፣ ውብ ተፈጥሮ፣ የከተማ ልማት ሥራና የእንግዳ ተቀባይነት ባህል የሚያሳይ ነው ተብሏል።
በመክፈቻው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ነብዩ ተድላ፣ በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓቲካ እና የሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

ይህ አውደ ርዕይ በዋናነት የተዘጋጀው ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ለሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ፣ የባህል ክለብ አባላትና ተጋባዥ እንግዶች መሆኑ ተገልጿል።
ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትስስርና የባህል ልውውጥን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን የቱሪስት መስህቦች ለማስተዋወቅና የባህል ብዝኅነትን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ኢዜአ በዘገባው ጠቅሷል።