AMN – ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም
በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎችን፣ በተለይም ሴቶችን ለከፍተኛ የጤና እክል እየዳረገ የሚገኘው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፤ ተገቢው ጥንቃቄ ከተደረገ አስቀድሞ መከላከልና በቀላሉ መታከም የሚችል የጤና እክል ነው፡፡
ይህ የጤና ችግር የሚከሰተው ባክቴሪያዎች በሽንት ማስተላለፊያ ቧንቧ በኩል ወደ ውስጥ ገብተው መራባት ሲጀምሩ መሆኑን የጠቅላላ ቀዶ ህክምናና የዩሮሎጂ ሰብ-ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር አህመድ አበበ ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል፡፡
ኢንፌክሽኑ በወቅቱ ካልታከመ ከሽንት ከረጢት አልፎ እስከ ኩላሊት ድረስ በመዝለቅ ከፍተኛ የጤና ጉዳት የማድረስ አቅም እንዳለውም አስረድተዋል።

የኢንፌክሽኑን መነሻ ምክንያቶች በተመለከተ ዶ/ር አህመድ ሲያብራሩ፤ በተለይ የሴቶች የሽንት መውጫ ቧንቧ ተፈጥሯዊ ቅርጽ አጭር መሆን ባክቴሪያዎች ለመግባትና ለመራባት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የግል ንጽህና አጠባበቅ ጉድለት፤ ሽንትን ለረጅም ጊዜ መያዝ (መቋጠር)፤ እንደ ስኳር በሽታ ያሉ የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅምን የሚቀንሱ የጤና እክሎች ለበሽታው ዋነኛ መንስኤ መሆናቸውን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
አንድ ሰው በኢንፌክሽን መያዙን የተለያዩ ምልክቶች እንደሚታዩ የጠቀሱት ዶ/ር አህመድ፤ ከእነዚህም መካከል ሽንት በሚሸኑበት ወቅት የሚሰማ ከፍተኛ የማቃጠል ወይም የመውጋት ስሜት ዋነኛው እንደሆነ አብራርተዋል።
በተጨማሪም የሽንት ቀለም መደፍረስ ወይም ደም መቀላቀል፤ ተደጋጋሚ የሽንት ስሜት መኖር፤የሽንት ሽታ መለወጥ፤ የታችኛው የሆድ ክፍል ወይም የጀርባ ህመም ምልክቶች የታዩበት ሰው በአስቸኳይ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ይህንን የጤና ችግር አስቀድሞ ለመከላከል በቀን ውስጥ በቂ ውሃ መጠጣት ባክቴሪያዎች ከሰውነት ውስጥ እንዲወጡ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ዶ/ር አህመድ ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር ሽንትን ሳይቋጥሩ ስሜቱ በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ መሽናት፤ ከሽንት በኋላ የሚደረግን ጽዳት ከፊት ወደ ኋላ በማድረግ ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ እንዳይገባ መከላከል፤ አየር የሚያስገቡ ከጥጥ የተሰሩ የውስጥ ሱሪዎችን መጠቀም ውጤታማ መከላከያ መንገዶች መሆናቸውን ተጠቅሰዋል።
ኢንፌክሽኑ ወደ ኩላሊት ከተሰራጨ እንደ ከፍተኛ ትኩሳትና ማቅለሽለሽ ያሉ ከባድ ምልክቶችን ሊያስከትል ስለሚችል፣ ወቅታዊ ህክምና ማግኘት እንደሚገባ የዩሮሎጂ ሰብ-ስፔሻሊስቱ ዶ/ር አህመድ አበበ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው