አራዳን ከብክለትና ወንጀል ምንጭነት ወደ ማኅበረሰባዊ መበልጸጊያነት የቀየረ የልማት አቢዮት

You are currently viewing አራዳን ከብክለትና ወንጀል ምንጭነት ወደ ማኅበረሰባዊ መበልጸጊያነት የቀየረ የልማት አቢዮት

AMN – ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ለበርካታ ዓመታት የብክለት መገለጫና የወንጀል መፈጸሚያ ስፍራ ሆነው የቆዩ አካባቢዎች በልማት ተቀይረው ለቱሪስት መስህብነትና ለገቢ ማግኛነት ዝግጁ እየሆኑ ይገኛሉ።

በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የአራዳ ፓርክ ተመርቋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአራዳ ፓርክ መመረቅን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ፣ ቀድሞ እጅግ ጎስቋላ ፣ ለኑሮ የማይመች የነበረውን አካባቢ ወደ ምቹ ሁለ ገብ አገልግሎት ከባቢ መቀየሩን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል እነዚህ አካባቢዎች የብክለት መገለጫ ፣ ለአፍንጫ የሚሰነፍጡ እና ለጤና ጠንቅ የሆኑ ስፍራዎች የነበሩ ናቸው።

በተለይም ወንዝ ዳርቻው ለተለያዩ የጤና ችግሮች መንስኤ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ በአሁኑ ወቅት በተከናወነው የልማት ስራ ይህን ያስወገደና ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ደህንነት እና ክብር ቅድሚያ በሰጠ መልኩ መቀየሩን ገልጸዋል።

የወንጀል መፈልፈያ የነበሩ አካባቢዎች እንደ እሪ በከንቱ ፣ ዶሮ ማነቂያ ያሉ የወንጀል መገለጫ ስሞችን በመለወጥ ፣ አካባቢው መዝናኛ ፣ መናፈሻ ፣ ገቢ እና የስራ እድል ማግኛ እንዲሆን መደረጉን ነው ያብራሩት።

አካባቢው ለቱሪስት ስበት እና ለመዝናኛ ምቹ ከመደረጉ ባሻገር ስፍራው የንግድ ሱቆች ያሉበት በመሆኑ አዳዲስ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑበትና ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ሆኖ ተገንብቷል።

የአራዳ ፓርክ ልማት የአካባቢውን አስከፊ ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የነዋሪዎችን ሰብአዊ ክብር የሚመጥንና ለከተማዋ ተጨማሪ የቱሪስት ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስረድተዋል።

መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል በሰጠው ልዩ ትኩረት እየተከናወነ ባለው የልማት ስራ ቀደም ሲል በወንጀልና በብክለት ይታወቁ የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ ላይ የከተማዋ አዲስ ገጽታና የውበት ምንጭ ለመሆን በቅተዋል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review