አመራሩ ውጤታማነቱ ሊለካ የሚገባው በሰው ህይወት ላይ ባመጣው ለውጥ ሊሆን ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing አመራሩ ውጤታማነቱ ሊለካ የሚገባው በሰው ህይወት ላይ ባመጣው ለውጥ ሊሆን ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም

አንድ አመራር ወይም የስራ ኃላፊ ውጤታማነቱ የሚለካው በወረቀት ላይ በሚቀመጡ ሪፖርቶች ሳይሆን፣ በሰው ህይወት ላይ ባመጣው እውነተኛ ለውጥ መሆን እንደሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

ከንቲባዋ ይህን ያሉት ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር የ2018 በጀት ዓመት እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ወቅት ላይ ነው።

ከሰው ተኮር ተግባራት አንፃር አመራሩ ሊኖረው በሚገባ እሳቤ ዙሪያ ያብራሩት ከንቲባዋ፣ በህዝብ እና በመንግስት የስራ ኃላፊዎች መካከል ያለው ርቀት መሰበር እንዳለበት እና መቀራረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የህዝብን ኑሮ እሳቤ እና ሮሮ ለመረዳት፣ ላይ ላዩን መሄድ ሳይሆን፣ ወደ ህዝቡ ቀረብ ማለት፣ ጓዳውን እና የዕለት ተዕለት ኑሮውን በቅርበት መመልከት እና የህዝቡን ህይወት መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህ ሰው ተኮር እሳቤ በተግባር ሲተርጎም፣ ከተማሪዎች ምገባ ጀምሮ፣ የድሆችን ቤት መገንባትና ማደስ፣ የዜጎችን ኑሮ ማዘመን እና ከጎናቸው ቤተሰብ ሆኖ መቆምን እንደሚያካትትም ገልጸዋል።

ስራዎቻችን የሚመዘኑት፣ ሰውን ተጠቃሚ አድርገዋል ወይ? ሰውስ ተረድቶታል ወይ? በሚለው መለኪያ ሊሆን ይገባል ያሉት ከንቲባዋ፣ አመራራችን በዚህ ደረጃ መለወጥና የህዝቡ አካል መሆን አለበት በማለትም ተናግረዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review