AMN- ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም
ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ዜጎች አካላዊና አዕምሯዊ ብቃት በማጎልበት በሚሰሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ አብሮነትን በማጠናከር መተሳሰብ እንዲሰፍን የሚያደርግ አስተሳሳሪ ትርክት የሚገነባበት ታላቅ ዘርፍ ነው ሲሉ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዮ መሐመድ ገለጹ፡፡
በነገው ዕለት የሚካሄደው በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው “የዓለም አቀፍ ሲቲ ማውንቴን ውድድር” ማጀቢያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀውና “የአረንጓዴው መንገድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የብስክሌት ውድድር መነሻውን ቦሌ አትላስ አድርጎ ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ መኪዮ መሐመድ፣ መንግስት ለስፖርት ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ግልጽ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ህብረተሰቡ በስፖርቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ውብ ጎዳናዎች ላይ የሚካሄደው የ “ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ ዓለም አቀፍ ውድድር” ማጀቢያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ውድድር ሀገራዊ አቅማችንን ለዓለም የምናሳይበትና የአንድነታችንን ዜማ በብስክሌት ሰንሰለት የምናቀናጅበት ታላቅ ውድድር ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ ዛሬ ከፍታዋን እያደሰች ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊው፣ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መሪነት ላለፉት ጥቂት ዓመታት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሲተገበር የቆየው የኮሪደር ልማትና የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ መዲናዋ ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ምቹና ተመራጭ እያደረጋት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በታምራት ቢሻው