AMN – ሚያዝያ 25/2018 ዓ/ም
በመስቀል አደባባይ መነሻውን ያደረገውና ስመ-ጥር አትሌቶችን ጨምሮ ከ4ሺ 500 በላይ ሕዝብ የተሳተፉበት የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል።
ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመቀናጀት በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ፣ ለአሸናፊዎች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።
በዚህም መሠረት በውድድሩ አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አትሌት የ600ሺህ ብር ሽልማት ሲያገኝ ፣ ሁለተኛ የወጣው አትሌት የ250,000 ብር ተሸላሚ ሆኗል።
በተመሳሳይ በውድድሩ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አትሌት የ175ሺህ ብር ሽልማት ተረክቧል።

አሸናፊ አትሌቶቹ በሰጡት አስተያየት እንዲህ ያሉ የጎዳና ላይ ውድድሮች መዘጋጀታቸው የተሻለ የውድድር ዕድልና ብቃታቸውን የሚያሳድጉበት አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል።
የውድድሩ የጉዞ መስመር ከመስቀል አደባባይ ተነስቶ ለገሀርን፣ ብሔራዊን፣ ሰንጋ ተራን፣ ሜክሲኮንና ፒያሳን አቋርጧል።
በመቀጠልም በአራት ኪሎ በኩል በመታጠፍ መድረሻውን በድጋሚ በመስቀል አደባባይ በማድረግ ውድድሩ በሰላም ተጠናቋል።
የዛይድ የደግነት ሩጫ የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር በስፖርታዊ እንቅስቃሴውና በበጎ አድራጎት ይዘቱ በርካታ ነዋሪዎችን በማሳተፍ ረገድ ውጤታማ እንደነበር ተገልጿል።
በበረከት ጌታቸው