AMN – ሚያዝያ 25/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የተከናወነው ሰፊ የኮሪደር ልማት ሥራ የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለታላላቅ ስፖርታዊ ኹነቶችና ለጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ምቹና ዘመናዊ መድረክ መፍጠር ችሏል።
ከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን አጠናቃ ለነዋሪዎቿና ለዓለም አቀፍ እንግዶች ክፍት ካደረገች ወዲህ፣ የጎዳና ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በዓይነትና በብዛት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ይገኛሉ።
የልማት ፕሮጀክቱ በዋናነት ሰው ተኮር ለሆኑ ግንባታዎች ቅድሚያ በመስጠቱ፣ ቀደም ሲል ለሩጫም ሆነ ለብስክሌት ጉዞ እንቅፋት የነበሩ ጠባብና የተበላሹ መንገዶች ደረጃቸውን በጠበቁ አማራጭ መሠረተ ልማቶች ተተክተዋል።
በዚህም በልማቱ የተገነቡት ዘመናዊ መንገዶች፣ ሰፊ የእግረኛ መንገዶችና የብስክሌት መስመሮች መዲናዋ ለተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ያላትን ዝግጁነት በተግባር እያስመሰከሩ ነው።
በዓመቱ ውስጥ በደመቀ ሁኔታ ከተከናወኑ ውድድሮች መካከል ትላንትናና ዛሬ የተካሄዱት የሲቲ ማውንቴን ባይክ የብስክሌት ውድድር እና የዛይድ ደግነት 5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

የሲቲ ማውንቴን ባይክ የብስክሌት ውድድር ተወዳዳሪዎች ያለምንም ስጋትና መጨናነቅ በራሳቸው መስመር እንዲጓዙ ማስቻሉ አዲስ አበባን እንደ አውሮፓውያን ከተሞች ለብስክሌት ጉዞ ምቹ እያደረጋት መሆኑን አመላክቷል።
በሌላ በኩል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ያስተናገደው የዛይድ ደግነት ሩጫ የከተማዋን አዲስ ገጽታ ለዓለም ያስተዋወቀ ታላቅ መድረክ ሆኖ አልፏል።
ውድድሮቹ የተካሄደባቸው መንገዶች ምቹ መሆን ለተወዳዳሪዎችም ሆነ ለተመልካች ልዩ እርካታን የሰጡ ሲሆን፤ ይህም ከተማዋ ወደፊት ግዙፍ ዓለም አቀፍ ማራቶኖችን የማስተናገድ ሙሉ አቅም እንዳላት ማረጋገጫ ሆኗል።

እነዚህ ውድድሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ መታየታቸው ደግሞ አዲስ አበባ በአፍሪካ የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆንና የሀገርን መልካም ገጽታ ለመገንባት ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተካሄዱ የሚገኙት የጎዳና ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከውድድር ባለፈ የከተማዋ መገለጫና የባህል አካል እየሆኑ መጥተዋል።
ይህም መዲናዋን ወደ ተሻለ የዕድገትና የስልጣኔ ደረጃ የሚያሸጋግራት ነው።
በበረከት ጌታቸው