AMN- ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታላቅ አምባሳደር የሆነው የድምጻዊ መሐሙድ አሕመድ የክብር ሐውልት መርቀዋል።
ይህ የክብር ሐውልት የቆመው አርቲስቱ ለሀገር አንድነትና ለሰላም በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ዕውቅና ለመስጠት ነው።
መሐሙድ አሕመድ በ1950ዎቹ አጋማሽ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ የሙዚቃ ጉዞውን የጀመረ ሲሆን፣ በተለይም በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን ውስጥ የ”ትዝታ” ሙዚቃ ስልት ንጉሥ በመሆን ስሙን በደማቅ ቀለም ጽፏል።
በተለይም “ሰላም” የተሰኘው ሥራው የሀገር ፍቅርንና አንድነትን በማቀንቀን ረገድ በሕዝብ ዘንድ እንደ ብሔራዊ መዝሙር የሚታይ ተወዳጅነት አለው።

“ለሰው ልጆች ፍቅር ለሰው ልጆች ሰላም
ለሰው ልጆች በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ ” የሚለው ስንኝም በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፡፡
ታዲያ አርቲስቱ በሕይወት እያለ እንዲህ ዓይነት ታላቅ ክብር መሰጠቱ፣ ለወጣቱ የጥበብ ትውልድ ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥርና “ጥበብን በባለቤቷ ሕይወት ማክበር” የሚለውን አዲስ ባህል የሚያጎለብት ነው።
መሐሙድ አሕመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም “አረ መላ መላ ” የሚለው አልበሙ የኢትዮጵያን ባህልና ዜማ ያስተዋወቀ ድንቅ የጥበብ ሰው መሆኑ ይታወቃል።
በትዝታ መንግስቱ