የኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት የሆነው 85ኛው የአርበኞች የድል በዓል በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

You are currently viewing የኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት የሆነው 85ኛው የአርበኞች የድል በዓል በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

AMN – ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አርበኞች ፋሺስት ጣሊያንን በታላቅ ተጋድሎ ድል በማድረግ የአምስት አመታቱ የጨለማ ዘመን ያበቃበት 85ኛው የድል በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙ አርበኞችና የከተማዋ ነዋሪዎች ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ክብርና ለሕዝባቸው ነፃነት ሲሉ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የደረሰ ተጋድሎ አድርገዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አባት አርበኛ ሻምበል ዋኘው አባይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዓመታት የሉዓላዊነት ታሪክ ሊኖራት የቻለው በነፃነት አርበኞች ተጋድሎና መስዋዕትነት መሆኑን አውስተዋል።

በወቅቱ አባት አርበኞች በነፍስ ወከፍና በባህላዊ መሣሪያዎች በመደራጀት፣ ዘመናዊ ትጥቅ ይዞ የመጣውን የጠላት ጦር ድል በማድረግ ለሀገሪቱ ነፃነት ጽኑ መሠረት መጣላቸውን ገልጸዋል።

ሌላው አባት አርበኛ አቶ ታከለ ፊጡማ በበኩላቸው፤ በተለይም “እኔ” ከሚለው የግል ስሜት ይልቅ “እኛ” በሚል የአንድነት መንፈስ መታገላቸው ለድሉ ቁልፍ ሚና እንደነበረው አስረድተዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ለአሁኑ ትውልድ ልዩ ልዩ ጥሪዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በተለይም ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት በአንድነት መቆም እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ አባት አርበኛ ሻምበል አሰፋ ደስታ ናቸው፡፡

ሻምበል አሰፋ አክለውም፣ ትውልዱ ያለውን እውቀትና ችሎታ በአግባቡ በመጠቀም ድህነትንና ኃላቀርነት ለማሸነፍ መትጋት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሮማን ጌታቸው በበኩላቸው፤ የሀገርን ሉዓላዊነት በልማት ለማጽናትና ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት መሥራት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በዚህ ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርበኞች፣ የጦር ኃይሎች አባላት እና አመራሮች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review