AMN – ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር የተገነባውን መታሰቢያ ሃውልት መርቀዋል፡
በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያሳረፉት ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔርን የሚዘክር መታሰቢያ ሐውልት ዛሬ ተመርቋል።
ይህ የመታሰቢያ ሐውልት ደራሲው ለሀገሪቱ ሥነ-ጽሑፍ ዕድገት ያበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ለትውልድ እንዲተላለፍ ከማድረጉም በላይ፣ ለሥነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች የሚሰጠውን ክብር የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
ዘመን ተሸጋሪው ብዕረኛ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር በልብ-ወለድ ድርሰቶቹ፣ በአጫጭር ታሪኮቹና በጋዜጣዊ ዓምዶቹ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይም እንደ “ትኩሳት”፣ “ሌሊቱ ካለቀ በኋላ”፣ “አምስት ስድስት ሰባት”፣ “ቦርጭቃ” እና “እነሆ ጀግና” ያሉ ሥራዎቹ በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ መድረክ ላይ ስማቸው በጉልህ የሚጠቀስ የጥበብ ውጤቶች ናቸው።
ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ሚያዝያ 24 ቀን 1928 ዓ.ም ተወልደው፣ በሥነ-ጽሑፍ ዓለም ውስጥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ደማቅ ታሪክ ሲሰራ ከቆዬ በኋላ የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።
ዛሬ የተመረቀው ይኸው መታሰቢያ ሐውልትም የደራሲውን የሥራ ውጤቶችና የሕይወት ጉዞ ዘወትር ሲዘክር የሚኖር የታሪክ አሻራ ሆኖ ያገለግላል።
በሻምበል ምህረት