AMN – ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም
“አርበኝነት ለሀገር ህልውናና ለተባበረች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በተከበረው 85ኛው የአርበኞች የድል በዓል ላይ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዛዡ በመልዕክታቸው፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በማንኛውም ሁኔታ የሀገርን ሰላም ሊያውኩ የሚሹ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን የመመከት ሙሉ ብቃት ያለው ሰራዊት ባለቤት መሆኗን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በወታደራዊ እውቀቱ የላቀ፣ በአካል ብቃቱ አስተማማኝ እና ጠንካራ ወታደራዊ ስነ-ልቦና የተገነባለት የመከላከያ ሰራዊት እንዳላት አዛዡ ገልጸዋል።

ይህ ሰራዊት በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ከውስጥም ይሁን ከውጭ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን በብቃት መመከት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የመከላከያ ተቋሙ የጀግኖች አርበኞችን አደራ መወጣት የሚችል፣ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሰረት የሚጥል እና ብሄራዊ ጥቅምን የሚያስከብር የሰራዊት ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ቫይስ አድሚራሉ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሰራዊቱ በተሰለፈባቸው አውደ-ውጊያዎች ሁሉ ተደራራቢ ስኬቶችን በመጎናጸፍ የጠላቶችን ሴራ እያከሸፈ እንደሚገኝና ለሀገር ሉዓላዊነት አስፈላጊውን መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ አክለውም፤ ኢትዮጵያ እንደወትሮዋ ሁሉ በልጆቿ ተጋድሎና መስዋዕትነት ከነሙሉ ክብሯ ጸንታ እንድትቀጥል ሰራዊቱ ማንኛውንም ዋጋ እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ለዛሬው ሰላም፣ ነጻነት እና የሀገር ሉዓላዊነት መከበር መሰረት ለሆኑት ጀግኖች አርበኞች ያላቸውን ጥልቅ ክብርና ምስጋና በመግለጽ፤ በዓሉ የሀገራዊ ፍቅርና አንድነት ማጠናከሪያ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ