AMN – ግንቦት 02/2018 ዓ.ም
እናቶች የሚከፍሉት መስዋትነት፣ ውለታና ፍቅር የሚዘከርበት የእናቶች ቀን ዛሬ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ይከበራል፡፡
በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ፣ አሜሪካ፣ ፊሊፒንስ፣ ቬንዝዌላ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛንያ እና ከ80 በላይ ሃገራት የእናቶችን ቀን ያከብራሉ፡፡
ዛሬ በዓለም ላይ በተለያየ መልኩ የሚከበረው፣ የእናቶች ቀን በተለያዩ ባህሎች የዳበረ ታሪክ አለው።
የዛሬው ዕለት ወልደው ላሳደጉ እናቶች ብቻ ሳይሆን እንደ እናት በፍቅርና እንክብካቤ ላሳደጉ የእንጀራ እናቶች፣ አክስቶችና እህቶችም ጭምር ፍቅር የሚገለጽበት ነው።
“ስለ እናት ፍቅር መግለጽ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በርካቶች እናታችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል” ይላሉ፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በርካታ እናቶች የእናትነት ግዴታቸውን ለመወጣት በሥራ የተወጠሩ በመሆናቸው ብዙዎች እናቶችን በማመስገን፣ የተለያዩ ስጦታዎችን በማበርከት እንዲሁም እናቶቻቸውን በሥራ በማገዝ እለቱን ያከብራሉ፡፡
በተጨማሪም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የእናቶችን ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስል በማጋራት ቀኑን ማክበር የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ እናት የፍቅር ምንጭ እና የጽናት ተምሳሌት ስትሆን በተለይም ለልጆቻቸው የሚከፍሉት መስዋትነት ልዩ ነው፡፡
እናት የርህራሄ፣ የጽናትና ብርታት፣ የብርሃን እና የመምህርም ተምሳሌት ስትሆን ይሄንን የእናትነትን ክብርና የማይተካ ሚና ለማድነቅና ዕውቅና ለመስጠት በየዓመቱ የፈረንጆቹ ግንቦት ወር በገባ በሁለተኛው እሁድ የእናቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡
ይሄም እናቶች ለልጆቻቸው እና ለቤተሰባቸው የሚከፍሉት መስዋዕትነት እንዲታሰብ ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው፡፡
የእናቶችን ቀን አሁን ባለው መልኩ ከመከበሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በ16ኛው ክፍለ ዘመን “የእናት እሑድ” በመባል የሚታወቅ በዓል እንደነበር ይነገራል።
በሻምበል ምህረት