ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የ11 ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

You are currently viewing ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የ11 ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

AMN – ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አዲስ የተሾሙ የ11 ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ዛሬ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተቀብለዋል።

አምባሳደሮቹም በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜ ቆይታቸው ሀገራቱ ያላቸውን ሁለንተናዊ ትብብርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ኪንግደም አምባሳደር አብዱላህ ቢን ሀሰን አል-ዛህራኒ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አንድሬ ፖህ፣ የፖርቹጋል ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጆርጅ ፔሬራ ዶ ናሲሜንቶ፣ የናይጄሪያ አምባሳደር ናሲር አሚኖ፣ የስሪላንካ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኒርማላ ኢንዱማቲ ዲያስ ፓራናቪታና፣ የማላዊ አምባሳደር ክዋውሊ መሲስካ የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡት መካከል ናቸው።

በተጨማሪም የጋና አምባሳደር ማካሪዮስ አካንቢያናብ አካንቦንግ፣ የኡራጓይ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ማሪዮ አንጄል ሲልቫ ካስትሮ፣ የስሎቫኪያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ራስቲስላቭ ክሪዣን፣ የማዳጋስካር ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኦገስት ሪቻርድ ፓሬና እንዲሁም የኡዝቤኪስታን ሪፐብሊክ ተሿሚ አምባሳደር አሽራፍ ኾጃዬቭ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንቱ አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት ማብራሪያ፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከአምባሳደሮቹ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልፀዋል።

አምባሳደሮቹም በኢትዮጵያ በሚቆዩበት ጊዜ ሀገራቱ ያላቸውን ሁለንተናዊ ትብብርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በስኬት ያጠናቀቀችው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለአፍሪካ ተምሳሌት መሆኑን በመግለፅ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review