AMN-ግንቦት 4/2018 ዓ.ም
የዓለም አትሌቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጆን ሪድጊኦን እና የውድድር መስተንግዶ ጨረታ ኃላፊው ማርክ ኸርስት ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ እንደሚገቡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሳውቋል::
የዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ኃላፊዎቹ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ኢትዮጵያ በቀጣይ ልታስተናግድ በጠየቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች ዙሪያ ከፌዴራልና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ይህ ጉብኝት ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ አትሌቲክስ መድረክ ያላትን ከፍተኛ ስፍራ የሚያጠናክር እና ወደፊት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ያላትን አቅም የሚያሳይ ነው ብሏል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርቡ ያስተናገደችው የነሀስ ደረጃ ያለው የአንድ ቀን የግራንድ ፕሪ ውድድር በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ አድናቆት እንዳስገኘላት የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም ውድድሩ በቀጣይ አመት በወርቅ ደረጃ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል።
አዲስ አበባ ከተማ የበርካታ ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች መዳረሻ እንድትሆን የኢፌዴሪ መንግስት ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንደሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሰሩ መሆናቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ዓለም አቀፍ የሲቲ ማውንቴን ባይክ እና ዛይድ የደግነት ሩጫ በቅርቡ በአዲስ አበባ በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ውድድሮቹን በብቸኝነት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን መስጠቱ የሚታወቅ ነው።
በታምራት አበራ