ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸቸውን ለማጠናከር ቋሚ የሁለትዮሽ የምክክር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ

You are currently viewing ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸቸውን ለማጠናከር ቋሚ የሁለትዮሽ የምክክር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ

AMN- ግንቦት 3/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸቸውን ለማጠናከር ቋሚ የሁለትዮሽ የምክክር ማዕቀፍ ስምምነት በዋሽንግተን ዲሲ ተፈራርመዋል።

በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩ የጋራ ትግበራ የሚሹ የትብብር አድማሶችን በማስፋት በሁለትዮሽ ፣ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

የተፈረመው የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር በየዓመቱ አንዴ አዲስ አበባ ሌላ ጊዜ ዋሽንግተን የሚካሄድ ሲሆን የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባውን በጋራ የሚመሩት ይሆናል።

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የሁለትዮሹ መዋቅራዊ ምክክር ሦስት ምሰሶዎችን ያካተተ እንዲሆን ተስማምተዋል።

አንደኛው የኢኮኖሚ ብልጽግናን፣ንግድ እና ኢንቨስትመንት ነው። በዚህ ክፍል የሁለትዮሹን ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ትስስር የበለጠ ማጠናከር እና ኢንቨስትመንት እና ንግድን ለማስፋት ይሰራል።

ሁለተኛው የመከላከያ እና ጸጥታ ትብብርን ይመለከታል። በዚህ ክፍል የጸጥታ ጉዳይ ትብብርን ማጠናከር እና በጋራ የደኀንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተሳትፎን ማጠናከርን ያካትታል።

የመጨረሻውን እና ሦስተኛው ምሰሶ ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋትን የተመለከተ ነው።

በዚህ ክፍል የጋራ ጥቅምን እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላምንና ደኀንነትን የሚያስጠብቁ አካሄዶችን በመፈተሽ እና በትብብር መሥራትን ያረጋግጣል።

ይህ ቋሚ የሁለትዮሽ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚያስቀጥል እና የሚያጠናክር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review