AMN – ግንቦት 5/2018 ዓ.ም
በዓለም ዙሪያ የስኳር በሽታ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ የጤና ባለሙያዎች ማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤውን ሊቀይር እንደሚገባ ያሳስባሉ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የ2026 ከ540 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከበሽታው ጋር የሚኖሩ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በ2045 ወደ 700 ሚሊዮን ሊጠጋ እንደሚችል ተገምቷል።
በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ሁኔታ በሽታው በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የተቀነባበሩ ምግቦች ፍጆታ መጨመር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማነስና ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ዘይቤ መሆኑ ይገለጻል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ የሕመምተኞች ቁጥር ውስጥ ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት በዓይነት ሁለት (Type 2) የስኳር በሽታ የተጠቁ መሆናቸውን ለኤ ኤም ኤን የገለጹት ዶ/ር አማረ ጉልላት፤ በሽታው በዘር፣ በክብደት መጨመር፣ በደም ግፊትና በምግብ ምርጫ ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል አስረድተዋል።
የስኳር ሕመም ምልክቶች ሳይታወቁ ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉ የገለጹት ባለሙያው፤ ከፍተኛ የውሃ ጥማትና የአፍ መድረቅ፣ በሌሊት ተደጋጋሚ ሽንት፣ ያለበቂ ምክንያት የክብደት መቀነስና ድካም፣ የእይታ ብዥታና ቁስል ቶሎ አለመዳን ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የአኗኗር ዘይቤን መቀየር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሳይሆን፤ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ቃጫማ (ፋይበር) ምግቦችን ማዘውተር፣ የታሸጉ ምግቦችን መቀነስና በቀን ለ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግንና በቂ ውሃ መጠጣት የመሰሳሉ ልምዶችን ማዳበር ነው።
በተጨማሪም አልኮልና ሲጋራን በማስወገድ እንዲሁም በየጊዜው የደም ስኳር መጠንን በመለካት በሽታውን ተከትሎ ለኩላሊት፣ ለልብና ለዓይን ሕመም ከሚዳርጉ ውስብስብ ችግሮች መከላከል እንደሚገባ ዶ/ር አማረ መክረዋል።
በበረከት ጌታቸው