AMN- ግንቦት 10/ 2018 ዓ.ም
የመዲናችን የብልጽግና ጉዞ ስፋትና ጥልቀት የሚለካው፣ የከተማዋን እምብርት በማስዋብ ብቻ ሳይሆን፣ ትናንት በአግባቡ ያልተጠቀምንባቸውን ሀብትና አካባቢዎችን ዓይናችንን ገለጥ በማድረግ ተመልክተን የልማትና የዕድገት ማዕከል በማድረግም ጭምር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፣ ከ5 ዓመት በፊት፣ ምንም የሚታይ መሠረተ ልማት ያልነበረው የገላን ጉራ አካባቢ፣ ዛሬ ላይ የታሪክ ምዕራፉ ተቀይሮ የከተማችንን ሁለንተናዊ የልማት ከፍታና መዋቅራዊ ሽግግር የሚያሳይ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መስተጋብር ማዕከል ሆኗል ብለዋል።
ዛሬ በዚህ ስፍራ ያረፈው አሻራችን የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢውን ገጽታ እና የነዋሪዎቹን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ከስር መሠረቱ የለወጠ ነው ሲሉም አክለዋል።

ለአብነትም:-
1 . በአዲስ አበባ የመጀርያው እና ትልቁ ባለ 325 ሜትር ርዝመት እና 60 ሜትር ስፉት ዘመናዊ ድልድይ፣
2 . 21.73 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው (ቃሊቲ ቀለበት -ቱሉዲምቱ እና ቃሊቲ ቀለበት – ቂሊንጦ አደባባይ) የኢትዮጵያ የንግድ ኮሪደርን ያሳለጠ እና ቀጥታ ከአየር መንገድ ካርጎ የሚያገናኝ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማት፣
3 . የከተማችንን የመኖርያ ቤት አቅርቦት ችግር ለማቃለል አዲስ ከተማን የመገንባት ያህል የሆነ 60 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣
4. ከካዛንቺስ አካባቢ ለልማት ለተነሱ ነዋሪዎቻችን የገነባነው ምቹና የተቀናጀ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር የሚገኝበት፣

5- የኅብረተሰባችንን ጤና በላቀ ደረጃ ለመጠበቅ በከተማችን በትልቅነቱ ቀዳሚ የሆነው የገላን ትሯማ ሆስፒታል ግንባታ ፣
6- በአካባቢው ለዚሁ ልማት ለእርሻ ሲጠቀሙበት የነበረውን መሬት ለለቀቁልን አርሶ አደሮች የተቀናጀ ዘመናዊ የግብርና ልቀት ማዕከል ግንባታ፣
7 . መንፈስን የሚድሱ ሰፋፊ አረንጓዴ ስፍራዎች እና ፓርኮች፣
8. የስፓርት ማዘውተርያዎችና የልጆች መጫወቻዎች፣ ለእናቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥር የእንጀራ ፉብሪካ ግንባታ እና የመሳሰሉት የብልፅግና አሻራዎች ደምቀው አካባቢውን ከመሐል ከተማ የበለጠ ተመራጭ አድርገውታል ብለዋል።