AMN – ግንቦት 11/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም በከተማዋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ይህ ፕሮግራም በሀገር ውስጥ ካስመዘገበው ተጨባጭ ውጤት ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትላልቅ ተቋማትና ሀገራት ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና እውቅናን አግኝቷል፡፡
ስለፕሮግራሙ ስኬታማነት በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ምስክርነቶችና እውቅናዎች ተሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እና የተለያዩ የጥናት ተቋማት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የምገባ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በተማሪዎች ላይ ይስተዋል የነበረው የትምህርት ማቋረጥ ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ሌላው በአሜሪካ ብሔራዊ የሕክምና ቤተ-መጻሕፍት (PMC) ላይ በወጣ ጥናት መሰረት፣ የምገባ ፕሮግራሙ ከተጀመረ በኋላ በተማሪዎች ላይ ይታይ የነበረው የመቀንጨር እና የክሳት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡
በተለይም ከ5 እስከ 9 ዓመት ባሉ ሴት ህጻናት ላይ የነበረው የመቀንጨር መጠን ከ12.2% ወደ 7.8% ዝቅ ማለቱን በጥናት መረጋገጡ በጥናቱ ተገልጿል፡፡
ይህ ፕሮግራም ምግብ ለሚያበስሉ፣ ለሚያቀርቡና ለሚያጸዱ በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶችና ሴቶች በህብረት ስራ ማህበር ተደራጅተው ቋሚ የስራ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡
ፕሮግራሙ በትምህርት ቤቶች ከተጀመረው የተማሪዎች ምገባ በተጨማሪ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ያካተተ 29 የህዝብ ምገባ ማዕከላት የተገነቡ ሲሆን፣ ይህም በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ መመገብ የማይችሉ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸዉ ዜጎችን ክብር ባለው መልኩ ለመደገፍ አስችሏል።

የአዲስ አበባ የምገባ ፕሮግራም ሰው ተኮር እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ700 ሺ በላይ ተማሪዎችን ተደራሽ ማድረግ የቻለ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረትን ስቧል።
አዲስ አበባ በምገባ ፕሮግራሟ አማካኝነት በ2022 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ 133 ከተሞችን በመብለጥ በዘላቂ የአመጋገብ እና ስነ-ምግብ ዘርፍ የ8ኛው የሚላን ከተሞች የምግብ ፖሊሲ ስምምነት ወርቃማ ሽልማትን በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ ከተማ በተካሄደው መድረክ አሸንፋለች።
ይህን ሽልማት በማሸነፍም አዲስ አበባ ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ ከተማ መሆን ችላለች።
በተመሳሳይ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በጥቅምት ወር 2024 የሚላን ከተሞች የምግብ ፖሊሲ ስምምነት ሴክሬተሪያት ዋና ኃላፊ ፊሊፖ ጋቫዜኒ በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን እና የህዝብ ምገባ ማዕከላትን በአካል ጎብኝተዋል፡፡

ሀላፊው ከጉብኝታቸው በኋላ የአዲስ አበባ የምገባ ፕሮግራም እጅግ የሚያስደንቅ እና ወደ ሌሎች የዓለም ከተሞችም በሞዴልነት ሊወሰድ የሚችል ተሞክሮ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የከንቲባ አዳነች አቤቤ ቁርጠኝነትንም ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ትልቅ ተሞክሮ መሆን አንደሚችል ሀላፊው አክለው አንስተዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የኬኒያ የግሎባል አሊያንስ ፎር ኢምፕሩቭድ ኒውትሪሽን ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ማውሪን ሙኬታ በበኩላቸው ፕሮግራሙን ካዩ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ስራው በሀገሪቱ የወደፊት ትውልድ ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት እያደረገ ነው ብለዋል።
ማውሪን ሙኬታ ዛሬ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙት እነዚህ ህጻናት የነገዎቹ የሀገሪቱ ዶክተሮች፣ ጠበቃዎች እና መሪዎች ናቸው በማለትም የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡
በአስማረ መኮንን