AMN – ግንቦት 12/ 2018 ዓ.ም
አንዲት ድምጽ በሃገር ግንባታ ሂደት ዉስጥ ትልቅ ድርሻ ስላላት ገዢ ሃሳብ ያለዉን እና ለሃገር የሚበጀዉን የፓለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባም ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም ተካሂዶ ተጠናቋል።
በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ድምፅ መስጫ ካርድ ላልወሰዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በዩኒቨርስቲ ለሚገኙ ተማሪዎችና በካምፕ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በልዩ ሁኔታ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም አጠናቋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
መራጮችም በዲጂታል “ምርጫዬ” መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊየን 514 በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።
አስተያየታቸዉን ለኤኤምኤን የሰጡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተቀመጠዉ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተመዝግበዉ የምርጫ ካርድ መዉሰዳቸዉን በመግለጽ በምርጫዉ እለት ገዢ ሃሳብ ያለዉን እና ለሃገር የሚበጀዉን የፓለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸዉን ተናግረዋል፡፡
አቶ ዮናስ ይዘርጋው የተባሉ የመዲናዋ ነዋሪ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማኒፌስቷቸዉ ዙሪያ የሚያደረጉትን የምርጫ ክርክር በመከታተል ላይ መሆናቸዉን በመግለጽ ይህም የሚበጃቸዉን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ እድል እንደፈጠረላቸዉ ተናግረዋል፡፡

ወጣት ሰለሞን ጥበቡ በበኩሉ ገዢ ሐሳብ ያለውን እና ለሃገር የሚበጀዉን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ እለቱን እየተጠባበቀ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በምርጫ መሳተፍ የዲሞክራሲ ባህልን ከማዳበርና መብትን ከመጠቀም ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለዉ የጠቆሙት ነዋሪዎቹ በመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች በእለቱ ድምፅ በመስጠት የዜግነት መብታቸዉን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በወርቅነህ አብዮ