AMN – ግንቦት 12/ 2018 ዓ.ም
በመዲናዋ የተከናወኑ እና ተግባራዊ የተደረጉ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ከተማዋን ለሌሎች ለዓለም ከተሞች ተሞክሮ ሰጭ እና የልምድ ማእከል እንድትሆን አድርጓታል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በሃገር ገፅታ ግንባታ ላይ ለውጥ ያመጡ እና ደስተኛ ማህበረሰብ እንዲሁም ሃብት መፍጠር የቻሉ ናቸው፡፡
አዲስ አበባ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ከተሞች ባሻገር ለዓለም ከተሞች በመልካም ተሞክሮ ሰጭነት የምትጠቀስ ከተማ ናት፡፡
ተግባራዊ በሆኑ ስራዎች ምቹ ከተማ ከመፍጠር ባለፈ ሃብት መፍጠርና ኢኮኖሚያዊ እድገትም ማምጣት ተችሏል፡፡
ሃገራት ከተሞቻቸውን የተሻሉ ለማድረግ መዲናዋ ላይ ያለውን ተሞክሮ በመውሰድ በከተሞቻቸው ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያን ብሎም የመዲናዋን ገፅታ ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
በተለይም የከተማ እድሳት ሂደት ላይ ታሪክንና ቅርሶችን ጠብቆ ማደስ፣ የፓርኮች ሥራ፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የህጻናት ማቆያዎች ፣የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች፣ ተግባራዊ የተደረጉ የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች የዓለም ከተሞች ተምክሮ የወሰዱበት ነው፡፡
እነዚህ ስራዎች ለጤና ምቹ ከባቢ ከመፍጠር ባለፈ ለብዙዎች የሥራ እድል የፈጠሩ፣ የትራንስፖርት ስርዓትን ያሳለጡ በመሆኑ የዓለም ከተሞች ብዙ ተሞክሮ እየወሰዱ ይገኛል፡፡
በተለይም የመብራት፣ የስልክ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን አቀናጅቶ መምራት እንደሚቻልም ትምህርት የወሰዱበት ነው፡፡

በዚህም አዲስ አበባ ከተማ ከበርካታ የዓለም ከተሞች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከበርካታ የዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራርማለች።
ቤጂንግ፣ ኒው ዴልሂ፣ አንካራ፣ ሴኡል፣ ስቶክሆልም፣ ካይሮ፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና ሳን ፍራንሲስኮ፣ ዱባይ እና ባኩ ከተሞች አዲስ አበባ ከተፈራረመቻቸው ከተሞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የእህትማማችነት ስምምነቶቹ የየሀገራቱን ህዝቦች የባህልና የታሪክ ልውውጥ የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡
የሻምበል ምህረት