አዲስ አበባን ከዓለም ጋር ያስተሳሰራት የ“እህትማማች ከተሞች” ምስጢር…

You are currently viewing አዲስ አበባን ከዓለም ጋር ያስተሳሰራት የ“እህትማማች ከተሞች” ምስጢር…

AMN – ግንቦት 12/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና እና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መቀመጫ ብቻ ሳትሆን፣ ከዓለም ታላላቅ ከተሞች ጋር ያላት ትስስርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ይገኛል።

ከተማዋ እስካሁን ያደረገቻቸው የ“እህትማማች ከተሞች”ስምምነቶች በይስሙላ ሳይሆን ታሪካዊ ዓላማን መሰረት ያደረጉና የከተማዋን ሁለንተናዊ ገጽታ የቀየሩ ናቸው።

አዲስ አበባ ከታሪካዊና ሐይማኖታዊ ከተሞች እንደ ኢየሩሳሌም (እስራኤል) እና ካይሮ (ግብፅ) ጋር የነበራት የቆየ ግንኙነት ቅርሶችን በጋራ ለመንከባከብ ትልቅ ድልድይ ሆኗታል።

በሌላ በኩል ከፍተኛ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ከሚኖርባት ዋሽንግተን ዲሲ ጋር ያለው ስምምነት የሀገራችንን ባህል፣ ምግብና ኪነጥበብ በአሜሪካ እምብርት ለማስተዋወቅ ሰፊ እድል ፈጥሯል። የጀርመኗ ሌይፕዚግ ከተማም በሙዚቃ እና ጥበብ ልውውጥ ቀዳሚዋ ነች።

ከተማዋን በዕውቀት ለመገንባት ከቻይና ከተሞች ቤጂንግ እና ቾንግቺንግ ጋር የተደረገው ስምምነት በዘመናዊ ከተማ ፕላኒንግ፣ በትራንስፖርት ማኔጅመንት እና በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የስልጠና እድሎችን አስገኝቷል።

የቱርኳ አንካራ ከተማ በአስተዳደር ሰራተኞች አቅም ግንባታ ላይ ስትሰራ፣ ሌይፕዚግ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በምርምርና በተማሪዎች ልውውጥ ትተባበራለች።

እንደ ኢስታንቡል ያሉ ከተሞች ለቱርክ ባለሀብቶች መምጣት ትልቅ በር በመክፈት በሀገራችን የጨርቃጨርቅ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

እንደ ቤጂንግ፣ ሼንዘን እና ሻንጋይ ያሉ የቻይና ከተሞች ደግሞ ለአዲስ አበባ የኢንዱስትሪ ዞኖች መስፋፋትና ለታላላቅ መሰረተ ልማቶች እንደ ቀላል ባቡር የፋይናንስ እና ቴክኒክ ድጋፍ መገኛ ሆነዋል።

የደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ደግሞ በፋይናንስ አስተዳደር ዙሪያ ልምድ ታጋራለች።

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን እነዚህ ስምምነቶች ትልቅ አቅም ሆነዋል።

በተለይም ከዱባይ ጋር ያለው ግንኙነት ከተማዋን ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሆቴል ዘርፉን ለማሳደግ እና አሁን ላይ ለሚታዩት የከተማ ውበትና ለኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ትልቅ የተሞክሮ ምንጭ ሆኗል።

ከጎረቤት አገራት ከተሞች እንደ ጅቡቲ እና ካርቱም ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ቀጠናዊ ሰላምን ለመጠበቅ እና የድንበር አካባቢ ህዝባዊ ትስስርን ለማጠናከር የታለሙ ናቸው።

እንደ ናይሮቢ እና ጆሃንስበርግ ያሉ ከተሞች ደግሞ የአፍሪካውያንን የወንድማማችነት ወዳጅነት የሚያጸኑ ሲሆን፣ የታሪካዊቷ የሩሲያ መዲና የሞስኮ ግንኙነትም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የጋራ መግባባትን የሚፈጥር ነው።

አዲስ አበባ ሰሞኑን ከአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ጋር በከተማ ልማት፣ በአገልግሎት ዲጂታላይዜሽን፣ በቤት ልማት፣ በቱሪዝም፣ በስፖርት እና በሁለቱ ህዝቦች መካከል የባህልና የታሪክ ልውውጥን የሚያጠናክር የእህትማማች ከተማ ስምምነት አድርጋለች፡፡

የአዲስ አበባ የ“እህትማማች ከተሞች”ስምምነቶች ከተማዋ ካላት ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግዝፈት አንጻር የተቃኙ ሲሆን፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም እና በኢኮኖሚ ረገድ ትልቅ አጋዥ እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review