የለሚ ገበያ ማዕከል የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የለሚ ገበያ ማዕከል የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ግንቦት 13/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለልና የግብይት ስርዓቱን ለማረጋጋት ታሳቢ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በተለይም በከተማዋ እየተካሄደ ካለው ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የህዝብን ቅሬታና ጥያቄዎች በዝርዝር ለመፍታት ታስቦ የተገነባው 7ኛው የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከል በሰሚት ዋና መንገድ ላይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

ከንቲባዋ አዲስ የተገነባውን የለሚ ገበያ ማዕከል አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፣ ማዕከሉ አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት ረገድ ትልቅ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ አስታውቀዋል።

ይህም ልማቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተና ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግስት ለዚህ ማዕከል ብቻ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ አምራቾች ከገበያ ዋጋ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ አድርገው እንዲሸጡ መመሪያ መቀመጡንና ይህም በቀጥታ ሸማቹን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ምርቶቹ ያለ ደላላና ያለ ምንም ተጨማሪ የኬላ ክፍያ ቀጥታ ከአምራች እጅ ለገበያ እንደሚቀርቡም አክለዋል።

በከተማዋ አጠቃላይ የኑሮ ውድነትን ታሳቢ ያደረገ በዓመት እስከ 18 ቢሊየን ብር የሚደርስ በጀት ለተለያዩ የድጎማ አገልግሎቶች መመደቡን የገለጹት ከንቲባዋ፣ ድጎማው ለጤና መድህን፣ ለዳቦ ፋብሪካዎች፣ ለትራንስፖርትና መሰል መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚውል መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ወደ ገበያ ማዕከላት መጥተው መገልገል የማይችሉ በጉብዝናቸው ወራት ሀገርን ያገለገሉ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን ለመደገፍ 29 የምገባ ማዕከላት ተቋቁመው ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ለህዝብ የማይሰራውን ቃል አይገባም፤ የገባውንም ቃል ይፈጽማል ያሉት ከንቲባዋ፣ ነዋሪዎች እነዚህ የተገነቡ የገበያ ማዕከላትን እንደ ራሳቸው ንብረት በመቁጠር እንዲጠቀሙባቸውና እንዲንከባከቧቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review