አዲስ አበባ እና ከዘመናዊ ህንጻዎች በስተጀርባ ያለው የህይወት ፍልሚያ

You are currently viewing አዲስ አበባ እና ከዘመናዊ ህንጻዎች በስተጀርባ ያለው የህይወት ፍልሚያ

AMN ግንቦት 14/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መገኛ ብቻም አይደለችም ፤ የሃገሪቱ ዋንኛ የማሕበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሥበት ማዕከልም ነች፡፡

አዲስ አበባ እንደዛሬው ውብ አበባን የመሰለ ገጽታን ከመላበሷ በፊት ጉራማይሌ መልክ የነበራት መዲና መሆኗ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በአንድ ወገን ዘመናዊ ሕንጻዎች ፤ በሌላ ወገን ያረጁ ፣ ያፈጁና የተጎሳቆሉ መንደሮች የሚታዩባት መዲና፡፡ በዚህ በኩል የተንጣለሉ ህንጻዎችና ቪላዎች ፤ በዚያ ማዶ ደግሞ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ያደረጉ ፣ በተበጣጠሱ ፕላስቲኮች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ያሉባት ከተማ፡፡

በዚህ በኩል እጅግ ጫፍ በረገጠ የኢኮኖሚ ደረጃ ሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው ተደስተውና ተንደላቀው የሚኖሩ ዜጎች የሚኖሩባት ፤ በዚያ ማዶ በቆሻሻ መሃል የእለት ጉርሳቸውን ፈልገው የሚኖሩ ወገኖች የሚኖሩባት መዲና ነበረች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ እና የነዋሪዎቿ የዘመናት ታሪክ በእነዚህና በሌሎች የኢኮኖሚና የኑሮ ደረጃዎች የሚገለጽ ቢሆንም እስከ ቅርብ አመታት ጊዜ ድረስ ግን ከዘመናዊ ህንዎችና ቪላዎች በስተጀርባ በተጎሳቆለና እጅግ መራር በሆነ ሕይወት ውስጥ ስለሚኖሩ ዜጎች ያሰበም ሆነ የተጨነቀ መሪም ሆነ መንግስት አልነበረም፡፡

በዘመናዊ ከተማ መሃል በተጎሳቆሉ ጭቃ ቤቶች፤ ቆርቆሮዎችና ፕላስቲኮች ውስጥ የሚኖሩ የመዲናዋ ነዋሪዎችም ችግሩንም ደስታውንም ችለው ከመኖር ውጪ ይህ የዘመናት የድህነት ታሪክ ይቀየራል የሚል ተስፋ አልነበራቸውም፡፡

እነዚህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ እንዲሁ ነዋሪዎች ብቻ ተብለው በቀላሉ የሚገለጹ ሳይሆኑ በአንድ ወቅት ሃገራቸውን በክብር ያገለገሉ፤ ለሃገርና ለወገናቸው ታላቅ ውለታ የዋሉ፤ ወልደው አስተምረው ልጆቻቸውን ለክብር ያበቁ ዜጎች ናቸው፡፡

ድህነት፤ የሰው ልጆች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ አምርረው የሚታገሉት የህይወት ምዕራፍ ቢሆንም እነዚህ ዜጎች ግን በተለያዩ ምክንያቶች ድህነትን ማሸነፍ ተስኗቸው የሰው ልጆችን ክብር በማይመጥን ሕይወት ውስጥ ለአመታት የኖሩ ናቸው፡፡

ከረጃጅም ህንጻዎች በስተጀርባ ሆና ስሟ እና ግብሯ ያልተጣጣሙላት አዲስ አበባ ጎዳናዎቿና ወንዞቿ በቆሻሻ የተሞሉና ለአይንም ለአፍንጫም የማይመቹ ዋንኛ የጤና ጠንቅ ነበሩ፡፡

በርካቶች አዲስ አበባ… አዲስ አበበባ ብለው የዘመሩላትና የዘፈኑላት አዲስ አበባ ለረጅም አመታት ስሟን ከግብሯ ጋር የሚያጣጥምላት ልጅ አጥታ በዚሁ በድህነት ታሪክ ውስጥ ከርማለች፡፡

ከለውጡ ወዲህ ግን በአዲስ አበባ የተከናወኑት በርካታ የልማት አብዮቶች በዘመናዊ ህንጻና ባረጁና ባፈጁ ቤቶች መካከል ያለውን ጉራማይሌ ገጽታንና የመዲናዋን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ የቀየሩ ብቻ ሳይሆኑ የበርካታ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታንም ቀይረዋል፡፡

በእነዚያ ለሰው ልጆች ክብር በማይመጥኑ ቤቶች ዉስጥ ሲኖሩ የነበሩ ዜጎች ዛሬ ላይ በተሻለ ቤት ውስጥ የመኖር እድል ማግኘት የጀመሩ ሲሆን ጧሪና ደጋፊ የሌላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎችም የተሻለ ቤትና ሰፈር ከመኖር አልፈው ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ትኩስና ንጹህ ምግብ ከበራፋቸዉ ላይ ማግኘት ችለዋል፡፡

አንዳንድ የመዲናዋ ባለሃብቶች ፣ የግልና የመንግስት ቷቋማትም እንደትናንትናው ምስኪን ወገኖቻቸውን እያዩ እንዳላየ የሚያልፉ ሳይሆኑ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም የአቅመ ደካማ ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚረባረቡ ለመሆን በቅተዋል፡፡

መዲናዋን ብቻ ሳይሆን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት እየቀየረ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ የልማት አብዮት አሁንም ድረስ በድህነት ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ትልቅ ተስፋን ሰንቋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ “አዲስ አበባን እንደ አዲስ” በተሰኘው መጽሃፍ ምረቃ ላይ የመዲናዋን ልማት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት አንዳንዶች ልማቱን ስንጀምር አዲስ አበባ ስለማትለወጥ በከንቱ አትድከሙ ብለው ሲመክሩን ነበር፤ ነገር ግን አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ እና አበባ እናደርጋታለን ብለን ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት በፈተና እሳት ውስጥ አልፈን ያቀድነውን ተግብረናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመፅሐፉ ውስጥ የታተሙት ቁጥሮችና ፊደላት ፣ የአዲስ አበባን ለውጥ በዝምታ የሚናገሩ ታሪኮች ናቸው፤ እያንዳንዱ ገፅ የምኞታችንን ልክ ብቻ ሳይሆን ፣ ያንኑ ምኞት መሬት ለማውረድ የለፋነውን ልፋትና ውጤት የሚዘክሩ ናቸው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review