የአረፋ እሴቶች ከመንፈሳዊ በረከትእስከ ብሔራዊ አንድነት

You are currently viewing የአረፋ እሴቶች ከመንፈሳዊ በረከትእስከ ብሔራዊ አንድነት

የዒድ አል አድሃ- አረፋ በዓል  በታላቅ መስዋዕትነት፣ በጽናት እና በተግባራዊ እኩልነት ላይ የተመሰረተ ጥልቅ መንፈሳዊና ማህበራዊ አንድምታ ያለው በዓል ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ሳይለያዩ በአንድነት የሚያከብሩት ይህ በዓል፣ የሰው ልጅ የእርስ በእርስ መደጋገፍና መደማመጥ በተግባር የሚታይበት ታላቅ ዕለት ነው። በዓሉ በውስጡ የያዛቸው የመስዋዕትነት፣ የመተሳሰብ፣ የይቅርታ እና የርህራሄ እሴቶች የሰው ልጆችን ትስስር የሚያጠናክሩ ከመሆናቸውም በላይ፣ ካለፈ ቁርሾ ይልቅ ለወደፊት ዕርቅና ሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ የሚጠቁሙ ህያው አስተምህሮዎች ናቸው። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም የአረፋ በዓል አንኳር እሴቶችን መነሻ በማድረግ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑትን ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚልን በማነጋገር  አጭር ዳሰሳ አድርጓል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በታሪክ ምርምር ረገድ ካላቸው ሰፊ እውቀትና ልምድ በመነሳት፣ የአረፋ በዓልን ኃይማኖታዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊና ታሪካዊ አንድምታውን ለዝግጅት ክፍላችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ በተለይም የግል ትውስታቸውን  ከበዓሉ መንፈሳዊ እሴቶች ጋር በማቆራኘት፣ በዓሉ የግል በረከት ብቻ ሳይሆን ለህዝቦች ትስስርና ለአብሮነት ያለውን ሚና በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡ እሳቸው የአረፋ በዓል የሚያስተምረን የመስዋዕትነት እና የታማኝነት እሴት እንደ ሀገር በጋራ ለምንቆምላቸው ጉዳዮች ትልቅ ስንቅ የሚሆን ነው፡፡ በተለይም እንደ ቀይ ባህር ባሉ ስትራቴጂካዊና ብሔራዊ ፋይዳ ባላቸው የጋራ አጀንዳዎች ላይ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና እድገት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የታሪክ ምሁሩ እንደነዚህ ያሉ በዓላት ልዩነትን ለማጥበብና የጋራ ጥቅምን ለማስከበር እንደ ትልቅ አጋጣሚ ልንጠቀምባቸው እንደሚገባ በማሳሰብ፣ ወቅታዊና ታሪካዊ ክስተቶችን ከሀገር ግንባታ ሂደት ጋር አዛምደው በዝርዝር አጫውተውናል፡፡

የአረፋ በዓል አንኳር እሴቶችና ሀገራዊ ፋይዳቸው

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል የዒድ አል አድሃ- አረፋ በዓል በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የመስዋዕትነት እና የታዛዥነት ተምሳሌት ነው ይላሉ። ይህ በዓል በውስጡ የያዛቸው እሴቶች ከአንድ እምነት ተከታዮች አልፈው፣ እንደ ሀገር በጋራ የሚያስተሳስሩንን አንኳር እሴቶች በውስጡ በመያዙ ፋይዳው መልከ ብዙ ነው፡፡ በበዓሉ የሚታየው የመረዳዳት እና የርህራሄ መንፈስ፣ ዜጎች በልዩነቶቻቸው ውስጥ ሆነው ለጋራ ዓላማ እንዲሰለፉ የሚያስችላቸው አቅም አለው ብለዋል።

የታሪክ ተመራማሪው አደም እንደተናገሩት፣ በዓሉ ከታላቁ የሐጅ ሥነ-ሥርዓት ጋር የተሳሰረ መሆኑንና ይህም የሰው ልጆች ሁሉ የእኩልነት መድረክ መሆኑን ያመለክታል። በዓረፋ ተራራ ላይ የሚደረገው ስብስብ የንጉሥ፣ የፕሬዝዳንት፣ የጄነራልም ሆነ የሰፊው ህዝብ ልዩነት የማይታይበት መሆኑን ያወሱት ምሁሩ፣ “ንጉሡም ይሁን ፕሬዝዳንት፣ ጄነራልም ይሁን መኮንን ሁሉም  በእኩልነት  አንዲት ሽርጥና አንዲት  ልብስ ለብሰው የሚውሉበት  እለት ነው” በማለት የሰው ልጅ በመሰረታዊነት አንድ መሆኑን አስረድተዋል።

የዒድ አል አድሃ- አረፋ በዓልን መነሻ በማድረግ የሚከወነው የሐጅ ሥነ-ሥርዓት ሌላው መገለጫ የሰው ልጅ ለፈጣሪው ያለውን ፍጹም ታዛዥነትና ሥነ-ምግባር ማሳየቱ ነው። ረዳት ፕሮፌሰሩ አያይዘው፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ካሉበት ርቀው፣ ስራቸውንና  ቤተሰባቸውን ትተው በአንድ ቦታ መሰብሰባቸው ከፍተኛ የዲሲፕሊን ውጤት ነው። “ንብረቱን እና ስራውን ትቶ፣ ከቤተሰቦቹ ርቆና በአንድነት ተሰባስቦ በዕለቱ ‘አቤት’ ብለው ጌታቸውን ይጠይቃሉ” በማለት፣ ለትልቅ ግብ ሲባል ጊዜያዊ የግል ጥቅሞችንና ምቾቶችን የመተው (የመስዋዕትነት) አስፈላጊነትን አብራርተዋል፡፡

ምሁሩ የአረፋን ተራራ ታሪካዊ አመጣጥ ከአደምና ሐዋ ዳግም መገናኘት ጋር በማያያዝ በዓሉን የዕርቅና የይቅርታ ተምሳሌት አድርገው ያቀርቡታል። አደምና ሐዋ ከገነት ከወጡና ከተለያዩ በኋላ በምድር ላይ የተገናኙበትና የፈጣሪን ምሕረት የተቀበሉበት መሆኑን ሲያብራሩ፣ “አረፋ ከስያሜው አደምና ሐዋን… አወቅሽኝ ወይ? አወቅከኝ ወይ? ተባብለው የተገናኙበት ቦታ ነው” በማለት፤ የጥል መጨረሻና የፍቅር መጀመሪያ መሆኑን ገልጸውልናል። ይህ የይቅርታ እሴት ለሀገራዊ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እንደ መሰረት ሊያገለግል የሚችል ሲሆን፣ ቂምን ሽሮ ለመደማመጥ ምቹ መንገድ ይከፍታል በማለት ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምሁሩ የዒድ አል አድሃ- አረፋ በዓል አላህ ለሰው ልጆች ምህረቱን የሚቸርበት ልዩ ቀን መሆኑን ያሰምሩበታል። በዕለቱ አማኞች ንብረታቸውንና ቤታቸውን ትተው በአንድ ሜዳ ላይ ተሰብስበው አምላካቸውን  ይለምናሉ። ረዳት ፕሮፌሰሩ ይህንን መንፈሳዊ ድባብ ሲገልጹ “አላህ ‘እነዚህን ባሮቼን እዩአቸው፤ በምድር ላይ ተሰብስበው ንብረታቸውን፣ ስራቸውን፣ ቤታቸውን ትተው እኔን ምህረት እየጠየቁ ስለሆነ ዛሬ ምህረት አድርጌላቸዋለሁ’ ብሎ የሚመሰክርበት እለት ነው” ይላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል አክለውም፤ በዓሉ ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የሰው ልጆች ሁሉ የእኩልነትና የአንድነት መድረክ መሆኑን አብራርተዋል። የዒድ አል አድሃ- አረፋ  በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚያስተላልፈውን የእኩልነትና የአንድነት መልዕክት ያጎላሉ። በበዓሉ  የሚደረገው ሥነ ስርዓት የሰው ልጅን መዳረሻና ከሞት በኋላ ያለውን ሁኔታ የሚያስታውስ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህንንም ሲያጠቃልሉ “ይህ ጸሎት አንድነትን፣ ህብረትን ነው የሚያሳየው… ሀብት ጥቅም የለውም፣ ዝና የለውም፤ በመሆኑም ሰው ሁሉ እኩል መሆኑን የሚያስተምር ነው” በማለት፤ በዓሉ ከመንፈሳዊነቱ ባለፈ ማህበራዊና ሰብዓዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የታሪክ ምሁሩ አጽንኦት የሰጡት አንዱ ጉዳይ፣ የሰው ልጅ በሙሉ ከአንድ ምንጭ የተገኘ መሆኑንና ልዩነቶች ለውበትና ለዕውቀት እንጂ ለጠብ ሊሆኑ እንደማይገባ ነው። ፈጣሪ ሰውን ሁሉ እኩል አድርጎ መፍጠሩን፣ እንዲሁም ለሰው ልጅ አስፈላጊውን ሁሉ መለገሱን በመጥቀስ፣ ይህንን ፀጋ ለበጎ ተግባር ማዋል እንደሚገባ የበዓሉን አንኳር እሴቶች መነሻ በማድረግ ይመክራሉ። ምሁሩ አክለውም “ሰው ማለት የፈጣሪ ተወካይ ነው፤ በመሆኑም በመሬት ላይ፤ ትልቅ አደራ የተረከበ ነው”። በመሆኑም የዒድ  አል አድሃ- አረፋ በዓል ትርጉም የሚኖረው እነዚህን  የመከባበር፣ የመረዳዳትና የእኩልነት እሴቶችን በተግባር  ስንተረጉማቸው መሆኑን ምሁሩ በአጽንኦት ገልጸዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በሀገር ውስጥና በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያሳለፏቸውን የዓመታት ተሞክሮዎች መነሻ በማድረግ፣ የዓረፋ በዓል በየትኛውም አውድ ቢከበር መሰረታዊ ይዘቱ አንድ መሆኑን ያስረዳሉ። በዓሉ ለዘመናት የዘለቁ ትውስታዎችን የሚያጭር ከመሆኑም በላይ፣ አማኞች “እኔ እበልጥ” የሚል የፉክክር መንፈስን አስወግደው በፈጣሪ ፊት በእኩልነት የሚቆሙበትና ምህረትን የሚማጸኑበት ቅዱስ ዕለት ነው። እንደ ምሁሩ ገለጻ፣ ይህ ዕለት የግል መንፈሳዊ እርካታ የሚገኝበት ብቻ ሳይሆን፣ የመስዋዕትነትን ትርጉም በተግባር በመተርጎም ለሌሎች ርህራሄ የሚታይበትና የእርስ በእርስ መደማመጥ ባህል የሚጎለብትበት ልዩ አጋጣሚ ነው።

ይህንን መንፈሳዊ እሴት ከኢትዮጵያዊያን ማህበራዊ ህይወት ጋር በማቆራኘት፣ የመረዳዳት ባህል በውስጣችን  ያለ እሴት መሆኑን የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል  ያነሳሉ። ሆኖም እንደ ዓረፋ ባሉ ታላላቅ በዓላት ወቅት ለተቸገሩ ወገኖች እጅን መዘርጋትና ደግነትን ማሳየት ከፍላጎት በላይ የሆነ ኃይማኖታዊና ግብረገባዊ ግዴታ መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻሉ። ይህ የመረዳዳት እሴት ከግለሰብ አልፎ ማህበረሰባዊ ትስስርን የሚያጠናክር በመሆኑ፣ በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በማሰብና ለጋራ ሰላምና አንድነት  በጋራ በመቆም ሊሆን እንደሚገባ ምሁራዊ ምክራቸውን ይለግሳሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ከበዓሉ ጋር በማስተሳሰር ከገለጹት አንዱ ጉዳይ፣ እንደ ወደብና  ቀይ ባህር ያሉ ስትራቴጂካዊ የሀገር ጥቅሞችን በዘላቂነት ለማስከበር በሚደረጉ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በጋራ መቆም ከህልውና ጋር የተያያዘ ነው የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ ግብጾች በናይል ጉዳይ ያላቸውን የማይናወጥ አንድነት እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፣ “እኛም እንደ ሀገር በባህር በር ጥያቄ ላይ ተመሳሳይ የጋራ አቋም ሊኖረን ይገባል” በማለት አስገንዝበዋል፡፡ ይህን ብሔራዊ ግብ ለማሳካት ደግሞ በአረፋ በዓል ወቅት የሚታየውን የግል ፍላጎትን ለላቀ ዓላማ የመሰዋት እሴት በተግባር ማዋል አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።

ዜጎች በፖለቲካዊ አመለካከታቸው የመለያየት መብት ቢኖራቸውም፣ እንደ ወደብ ባሉ የትውልድ ዕጣ ፈንታን በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ግን አንድ ልብ ሆነው ሊደማመጡ እንደሚገባ ነው ምሁሩ የሚገልጹት፡፡ በኃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሚታየው  የአንድነትና የጋራ መደማመጥ፣ ወደ ሀገራዊ ስትራቴጂካዊ ጥያቄዎች ሲመጣም የማይታለፉ የሚመስሉ መሰናክሎችን ለማለፍና የሀገርን ጥቅም ለማስከበር ትልቁ መሣሪያ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ፣ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ያጋሩን ሃሳብ እንደሚያመለክተው፣ የአረፋ በዓል ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባለፈ ለሀገር ግንባታና ለብሔራዊ አንድነት የሚረዱ ስንቅ የሆኑ እሴቶችን በውስጡ መያዙን ነው። በበዓሉ ላይ የሚታየው እኩልነት፣ የግል ጥቅምን ለላቀ ዓላማ የመሠዋት ልምድና  የይቅርታ ባህል፣ እንደ ሀገርም ልንጠቀማቸው እንደሚገባ ነው ምሁሩ በአጽንኦት የገለጹት። በተለይም እንደ ባህር በር ያሉ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን ለማስከበር በዓሉ የሚያስተምረውን በጋራ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ አንድነት መፍጠር እና የመደማመጥ እሴት ወደ ብሔራዊ አንድነት ማምጣት ይገባል። በመሆኑም፣ የአረፋን በዓል ስናከብር እነዚህን የቆዩ የሰላም፣ የርህራሄና የጽናት እሴቶች ከተግባራዊ ሀገራዊ ፍላጎቶቻችን ጋር በማስተሳሰር ለተሻለችና አንድነቷ ለጸና ኢትዮጵያ መሠረት ልናደርጋቸው እንደሚገባ ነው ምሁሩ ያስገነዘቡት።

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review