በፅናት የተገኘ ስኬት

You are currently viewing በፅናት የተገኘ ስኬት

ባለፉት ሀያ ሁለት ዓመታት፣ ዓለም በፖለቲካውም ሆነ በስፖርቱ መስክ ፈጣንና ግዙፍ ለውጦችን አስተናግዳለች። በዚህ ወቅት ባራክ ኦባማ የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ታሪክ ሲሰሩ፣ በታላቋ ብሪታንያ የነገሱት ንግሥት ኤልሳቤጥም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ዓለምን ያናወጠውና የአኗኗር ዘይቤን የቀየረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ አልፏል፤ የቴክኖሎጂው በብዙ እጥፍ ተራምዷል። ማህበራዊ ሚዲያዎች ዓለምን በአንድ መንደር አስተሳስረዋል፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ መንግሥታት ተለዋውጠዋል፡፡

በስፖርቱ ዓለምም እንዲሁ የሊዮኔል ሜሲና የክርስቲያኖ ሮናልዶ አስደናቂ የፉክክር ዘመን ተጀምሮ አብቅቷል። የአርሴናል የከተማ ተቀናቃኝ ቼልሲ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ሌስተር ሲቲ ሳይቀሩ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በተደጋጋሚ ሲያነሱ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ዩሴይን ቦልት ያሉ አትሌቶች የስፖርቱን ዓለም አዲስ ታሪክ ፅፈው አልፈዋል። አልፎ ተርፎም የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ተጫዋችነቱን አቁሞ፣ አሰልጣኝ ሆኖ፣ በርካታ ዋንጫዎችን መሰብሰብ ችሏል። ነገር ግን፣ ይህ ሁሉ የዓለም ግዙፍ የለውጥ ሂደት ሲከናወን አንድ ነገር ሳይሳካ ቆይቷል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪካዊውና በዓለም ላይ ሚሊዮኖች የሚደግፉት የአርሴናል እግር ኳስ ክለብ ከዋንጫ አሸናፊነት ርቆ ቆይቷል፡፡

የአርሴናል እግር ኳስ ክለብ የመጨረሻውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በታሪካዊው የ“ማይሸነፉት” (The Invincibles) ስብስብ አማካኝነት ሲያነሳ ዘመኑ የዛሬ 22 ዓመት፤ የ2003/04 የውድድር ዓመት ነበር። የቡድኑ የልብ ትርታና የለንደኑ ተወዳጅ ኮከብ ቡካዮ ሳካ በ2004 ዓ.ም የሁለት ዓመት ከግማሽ የወተት ጥርስ ሕፃን ነበር። በፈረንሳዩ ‘ሌኪፕ’ ጋዜጣ የድሉ “እውነተኛ ልብ” ተብሎ የተወደሰው ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ ደግሞ ገና የሶስት ዓመት አዳጊ ነበር፡፡ ቡድኑን በአምበልነት መርቶ ለክብር ያበቃው ማርቲን ኦዴጋርድ እንደዚሁ፣ የ5 ዓመት አዳጊ ነበር። ይህ የጊዜ ንጽጽር እውነት፣ እግር ኳስ የማያቋርጥ የትውልድ ቅብብሎሽ መሆኑን ነው።

እ.ኤ.አ በ2004 በአርሴን ቬንገር መሪነት ዓመቱን ሙሉ ሳይሸነፍ ‘The Invincibles’ ተብሎ በታሪክ የወርቅ ቀለም ከጻፈበት ጊዜ በኋላ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሴናል ያሳለፈው ጊዜ በፈተናዎች የተሞላ ነው። ከሃይበሪ ወደ ኤምሬትስ ስታዲየም የተደረገው ሽግግር ክለቡን ለዓመታት ለከፍተኛ ዕዳ በመዳረጉ አርሴናል ኮከብ ተጫዋቾችን ለመሸጥ ተገድዷል። በሊጉ ከታላላቆቹ አራት ውስጥ መግባት ባለመቻል የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ማጣት እና የደጋፊዎች ተስፋ መቁረጥ ክለቡን ክፉኛ ፈትነውት ቆይተዋል። ባለፉት ጥቂት የውድድር ዓመታት ደግሞ ዋንጫውን ለመጨበጥ ተቃርበው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በማንቸስተር ሲቲ ሲነጠቁ የነበረው የደጋፊዎች ስሜት እጅጉን ሲጎዳ ቆይቷል።

በለንደን ከተማ ብቻም ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክለቡ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ የነበረውን የ22 ዓመታት የዋንጫ ጥም በ2026ቱ የውድድር ዓመት ምላሽ አግኝቷል፡፡ በ37ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ በበርንማውዝ ሜዳ አንድ አቻ መለያየቱን ተከትሎ፣ የሰሜን ለንደኑ አርሴናል እ.ኤ.አ ከ2004 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል። ይህ ድል ለ22 ዓመታት የዘለቀ የናፍቆት፣ የልብ ስብራት፣ የትዕግሥት እና የፅናት መገለጫ ነው ሲሉ ብዙዎች ይገልፁታል።

አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የክለቡን መንበር ሲረከቡ ቡድኑ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብቶ ነበር። ወጣቱን ስብስብ በመገንባት፣ የክለቡን ባህል በመቀየር እና በደጋፊው እና በቡድኑ መካከል የነበረውን የሻከረ ግንኙነት በመጠገን ረጅም መንገድ ተጉዘዋል። ቡድኑ በተደጋጋሚ ሲወድቅ እና ሲነሳ፣ ትችቶች ሲበራከቱ፣ አርቴታ ግን “ሂደቱን እመኑ” (Trust the Process) በሚል መርሕ ተጓዙ። ይህ መርሐቸው በተፈለገው ፍጥነት ውጤት ባለማምጣቱ ብዙዎች እንዲያሾፉባቸውም አድርጓቸው ነበር።

ዛሬ ላይ “ሂደቱን እመኑ” የሚለው መርሐቸው ፍሬ አፍርቶ የአርሴናል የሊጉን ዋንጫ የመጠበቂያ ጊዜው አከተመ። አርቴታ የተማመኑባቸው ወጣቶች እምነታቸውን አልበሉም፤ የሳካ ድንቅ ብቃት፣ የኦዴጋርድ መሪነት እና የመላው ቡድን አንድነት ለአርሴናል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል። በውጤቱ ከለንደን እስከ አዲስ አበባ፣ ከቶኪዮ እስከ ኒው ዮርክ በዓለም ዙሪያ ያሉ የአርሴናል ደጋፊዎች ወደር በሌለው በደስታ ባህር ውስጥ ናኙ፤ የደስታ ዕንባ ያፈሰሱም በርካቶች ናቸው።

ላለፉት 22 ዓመታት በሌሎች ክለቦች ደጋፊዎች ይደርስባቸው የነበረውን ስላቅ እና ብሽሽቅ በትዕግሥት ያሳለፉት የአርሴናል ደጋፊዎች በኩራት አንገታቸውን ቀና ማድረግ ችለዋል። ጎልማሶች እና አባቶች ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ላሉ ወጣቶቹ “አርሴናል ዋንጫ ሲያነሣ እንዲህ ነበር” እያሉ የሚተርኩበት ዘመን አብቅቶ፣ አዲሱ ትውልድ የራሱን ታሪክ በዓይኑ ያየበት ወቅት ሆኗል። በለንደን ጎዳናዎች ላይ የሚታዩት ቀይ እና ነጭ ማሊያ የለበሱ ደጋፊዎች በደስታ ሲጨፍሩ፣ አንዳንዶቹም ላለፉት 22 ዓመታት ያሳለፉትን ውጣ ውረድ እያሰቡ የደስታ እንባ ሲያፈሱ ተስተውለዋል ይላል የ ዘ አትሌቲክ ዘጋባ።

ገና በ8 ዓመቱ ወደ አርሴናል አካዳሚ በመግባት “እዚህ ክለብ ውስጥ ኮከብ መሆን እፈልጋለሁ” ያለው የ24 ዓመቱ የክለቡ ምክትል ካፒቴን ቡካዮ ሳካ፣ ከ16 ዓመታት የልጅነት ጥረትና በ311 ጨዋታዎች ላይ ላበረከተው አስደናቂ የ152 የጎልና የጎል  አስተዋጽኦ የሊጉን ዋንጫ በመጨበጥ ትልቅ ምላሽ ሰጥቷል። ሳካ የሻምፒዮንነት ድል ማግስት ባስተላለፈው የቪዲዮ መልዕክት፣ “ለ22 ዓመታት ሲስቁብንና ሲቀልዱብን ነበር፤ ከዚህ በኋላ ግን አይስቁብንም!” በማለት ለዓመታት በክለቡና በደጋፊው ላይ ይወርድ የነበረውን ማሾፍና ስድብ ያበቃለት መሆኑን በኩራት ገልጧል፡፡

የቢቢሲ ስፖርት ተንታኝና የቀድሞ የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋች ሚካ ሪቻርድስ፣ ቡድኑ ያሳየውን የስነ-ልቦና ሽግግር ሲያደንቅ፣ “አርሴናል በመጨረሻ ከመሸነፍ ፍርሃት ወጥቷል። ይህ ቡድን አሁን እውነተኛ የአሸናፊ አዕምሮ ገንብቷል” ብሏል። ሪቻርድስ አክሎም፣ ይህ ውጤት በአንድ ጀምበር የመጣ ሳይሆን አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በተሰጠው ጊዜና ትዕግሥት ላለፉት ሶስት ዓመታት በጥንቃቄ የገነባው ድንቅ ፕሮጀክት ፍሬ መሆኑን መስክሯል።

የስካይ ስፖርቱ ተንታኝ ጋሪ ኔቪል በበኩሉ፣ ድሉ ለደጋፊው ማኅበረሰብ ያለውን ትርጉም በስሜት ገልጾታል። “ለአርሴናል ደጋፊዎች ለ22 ዓመት ሙሉ ተስፋ ሳይቆርጡ ቆይተዋል” ያለው ኔቪል፣ የሰሜን ለንደኑን ታማኝ ደጋፊዎች “በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ካሉ በጣም ታጋሽና ጽኑ ደጋፊዎች” ሲል አወድሷቸዋል። በሌላ በኩል፣ የዘ አትሌትክ ታዋቂው የእግር ኳስ ጸሐፊ ዴቪድ ኦርንስቴን፣ የክለቡን ጉዞ ለየት ባለ እይታ አስቀምጦታል። ኦርንስቴን ይህንን ታሪክ “በአንድ ወቅት ሂደቱን እመኑ እየተባለ ከሚሳለቁበት መድረክ ተነሥቶ፣ ዛሬ ወደ እውነተኛ የእግር ኳስ ፕሮጀክት የተቀየረ ታላቅ ታሪክ” ሲል አክብሮታል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የአርሴናልን የዓመታት ጉዞ “ከውድቀትና ከከባድ ፈተናዎች ተነስተው፣ ተስፋ ባለመቁረጥና በማይናወጥ ጥንካሬ ወደ እግር ኳስ ማማው ማደግ የቻሉበት ታላቅ ጀብዱ” ሲሉ አሞካሽተውታል። ክለቡ በየሳምንቱ ከተፎካካሪዎች ጋር ያደረገው ፍልሚያ የተስፋን፣ የፅናትን እና የጠንካራ ስራን ኃይል በተግባር ያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ “በደማቁ ምሽት ያ ታላቅ ጥረት ፍሬ አፍርቷል፤ ቡድኑም የድሉ ባለቤት ሆኗል። ይህ ድል በጠንካራ ስራ፣ በዲሲፕሊን እና በቡድን መንፈስ ስኬትን ማምጣት እንደሚቻል ማረጋገጫ ነው” በማለት ገልፀውታል፡፡

ለዓመታት ይወርድባቸው የነበረውን ነቀፌታና የጥርጣሬ አጥር ሰብረው ለመውጣት መድፈኞቹ ያሳዩት ፍልሚያ የእግር ኳስን ጥበብ ወደ ላቀ የህይወት ፍልስፍና የቀየረ ነበር። እያንዳንዱ ተጫዋች በሜዳ ላይ ሲታገልና ለአንድ ዓላማ በጋራ ሲቆም የነበረው ትዕይንት፤ ተስፋ በውስጡ ለሌለው ሰው ብርሃን የሚሰጥ፣ ፅናት ደግሞ አቋራጭ መንገድ ለሚፈልጉ ሁሉ ከባድ ስራን የሚሰብክ ድንቅ ማስተማሪያ ሆኗል። በመጨረሻም፣ ይህ ስብስብ የሊጉን የክብር አክሊል ሲቀዳጅ ያሳየው ትልቁ እውነት፣ በፅናት ከቀጠሉና ጠንክሮ መስራት ከተቻለ የማይታለፍ ተራራና የማይሰበር የጥርጣሬ ግንብ በምድር ላይ እንደሌለ ነው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review