የታዛዥነትና የአንድነት ተምሳሌት ታላቁ የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል

You are currently viewing የታዛዥነትና የአንድነት ተምሳሌት ታላቁ የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል

AMN – ግንቦት 17/2018 ዓ.ም

የዒድ አል-አድሃ ወይም የታላቁ የአረፋ በዓል ጥልቅ ማህበራዊና መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን ሰንቆ፣ ከታላቁ የሐጅ ጉዞና ከፍጹም እምነት ጋር በተያያዘ መንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራል።

የበዓሉ መነሻ ታሪክ የሚመዘዘው ከነቢዩ ኢብራሂም እና ከልጃቸው ከነቢዩ እስማዔል ፍጹም የፈጣሪ ታዛዥነት ገድል ጋር ነው።

የነቢዩሏህ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) የሚወዱትን ልጃቸውን መስዋዕት እንዲያደርጉ ከአላህ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ያለ ምንም ማንገራገር ለመፈጸም በተነሱበት ቅጽበት፣ ፈጣሪ ለታማኝነታቸው በግ በመላክ ልጃቸውን ተክቶላቸዋል።

ይህ ታሪካዊ ክስተት ሙስሊሞች ለፈጣሪ ያላቸውን ፍጹም ተገዢነት እና ለአላህ ሲሉ ውድ ነገራቸውን መስዋዕት ማድረግን በየዓመቱ እንዲያስታውሱ ያደርጋል።

የአረፋ በዓል ሃይማኖታዊ ክንውን ብቻ ሳይሆን፣ ማህበራዊ ፍቅርና አንድነት በተግባር የሚታይበት ነው።

በዚህ ቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሐጅ ተጓዦች በዓረፋ ተራራ ላይ በመሰብሰብ እጃቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ምሕረትን በጋራ ከፈጣሪያቸው ይለምናሉ።

በተለይም በዓረፋ ተራራ ላይ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሙስሊሞች “ኢህራም” የተሰኘውን ተመሳሳይ ነጭ ጨርቅ ለብሰው፣ ያለምንም የዘር፣ የቋንቋ እና የሀብት ልዩነት ጎን ለጎን መቆማቸው የሰውን ልጅ በፈጣሪ ዘንድ እኩል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ይህ ማህበራዊ ትስስር በበዓሉ ዕለት በሚከናወነው የመስዋዕት ስርዓት ላይም በግልጽ ይንጸባረቃል።

በበዓሉ ማለዳ የዒድ ሰላት ከተሰገደ በኋላ አቅም ያለው ሙስሊም ሁሉ እንደ በግ፣ ፍየልና ከብት ያሉ እንስሳትን ያርዳል።

ይህ የኡድሒያ መስዋዕት ለቤት ፍጆታ ብቻ የሚውል ሳይሆን፣ ማህበራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በሶስት እኩል ቦታ ይከፈላል።

የመጀመሪያው አንድ ሶስተኛ ለምስኪኖች እና ለነዳያን በምጽዋት መልክ የሚለገስ ሲሆን፣ ሁለተኛው አንድ ሶስተኛ ደግሞ ለዘመድ፣ ለጎረቤትና ለወዳጅ በስጦታ መልክ ይበረከታል፤ የቀረው የመጨረሻው አንድ ሶስተኛ ለቤተሰብ ምግብነት እንዲውል ይደረጋል።

ይህም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከራስ ወዳድነት ወጥቶ ለሌሎች እንዲያስብ፣ የተቸገሩትን እንዲረዳ እና ሰላምን፣ ፍቅርንና ማህበራዊ አንድነትን በተግባር እንዲያጠናክር የሚያደርግ የታዛዥነትና የአንድነት ተምሳሌት ነው።

የ1447ኛው ዓመተ ሒጅራ (የ2018 ዓ.ል) የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል የፊታችን ረቡዕ በእስልምና እምነት ተካታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሮ ይውላል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review