AMN ግንቦት 23/2018

በአዲስ አበባ የሚገኙ የምርጫ ክልሎች የምርጫ የማስፈጸሚያ ቁሳቁስ ሥርጭት ተደራሽ በማድረግ ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።
ነገ በሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በየምርጫ ጣቢያዎች በመሰራጨት ዝግጁ እየሆኑ ይገኛሉ።

በዚህም የኢዜአ ሪፖርተር በመዲናዋ በምርጫ ክልል 2 እና 14 በአካል ተዘዋውሮ እንደተመለከተው፣ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ስር በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የማስፈጸሚያ ቁሳቁስ ስርጭት ተጠናቋል።
በምርጫ ክልል 2 እና 14 ስር 14 የምርጫ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን የምርጫ ቁሳቁሶቹ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽ በማድረግ ለምርጫው ሙሉ ዝግጅት መደረጉን መታዘብ ችሏል።