የአረንጓዴ መሠረተ-ልማቶች ለከተማ ገጽታና ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያበረክቱት ሚና

You are currently viewing የአረንጓዴ መሠረተ-ልማቶች ለከተማ ገጽታና ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያበረክቱት ሚና

AMN- ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስና ሥነ-ምህዳሩን ለመታደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች።

በተለይም በአረንጓዴ አሻራ፣ በደን ልማት እንዲሁም በከተማና ገጠር የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተተገበረው ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ 23.6 በመቶ ማሳደግ ማስቻሉን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል።

እንዲሁም የአፈር ጥበቃን ማጠናከር፣ የመስኖ አጠቃቀምን ማስፋፋትና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ሊስማሙ የሚችሉ ዘመናዊ የግብርና አሠራሮች በስፋት ተተግብረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚገኝ ሲሆን ይህንን ንጹህ ኃይል ወደ ትራንስፖርትና ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የማስፋፋት ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።

በተለይም የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት አዲስ አበባን ጨምሮ በ68 ከተሞች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በከተሞች የታየውን አመርቂ ውጤት በገጠሩም በመድገም የማኅበረሰቡን አኗኗር ለማሻሻል፣ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነው የሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታም ወደ ተግባር ተገብቷል።

አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ንጹህና ውብ ለማድረግ ከኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች በሻገር የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓትን የማሻሻል ተግባራት ተከናውነዋል።

ለአብነትም ከለውጡ በፊት በከተማዋ አንድ የፍሳሽ ማጣሪያ ብቻ የነበረ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ባከናወናቸው የተቀናጁ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት የፍሳሽ ማጣሪያ ማዕከላትን ቁጥር 43 ማድረስ ተችሏል።

በዚህም የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቷን በማዘመንም አዲስ አበባ በአፍሪካ ጽዱ ከሚባሉ 10 ቀዳሚ ከተሞች መካከል አንዷ ለመሆን በቅታለች።

በአጠቃላይ የከተማ አረንጓዴ መሠረተ-ልማቶች የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ከከተሞች የሚወጣውን የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት በመቀነስ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ53ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የዓለም የአካባቢ ቀን “በተፈጥሮ አነሣሽነት፣ ለአየር ንብረት፣ ለነገው ሕልውናችን” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።

የዓለም የአካባቢ ቀን ሲከበርም፤ የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚረዱ የፋይናንስ ምንጮችን ማፈላለግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን ማገዝና የእውቀት ማሳደጊያ አጋርነቶችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review