AMN- ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ግንባታው የተጀመረው የስማርት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ለሥራ ፈጣሪዎች እና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሞያዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ እድል ያሰፋል።
አስተዳደሩ ከ«ሰዎች ለሰዎች ድርጅት» ጋር በመተባበር የሚያስገነባው የስማርት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ግንባታ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተጀምሯል።
ኮሌጁ ግንባታው ተጠናቆ ስራ ሲጀምር ተግባር ተኮር ክህሎት ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች የገበያውን ፍላጎት የሚያሟላ ዘመናዊ ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ ያስችላል።
ከዚህ ባለፈም ስማርት ቴክኖሎጂዎችን እና ዲጂታል አሰራሮችን በሥራቸው ውስጥ ለመተግበር ለሚፈልጉ ባለሞያዎች አቅም የሚፈጥር ሲሆን፣ አዳዲስ አሰራሮች ወደ ስራ የሚገቡበትን እድልም ያሰፋል።

ባለሞያዎች እና አዲስ ስራ የሚጀምሩ ወጣቶችም ዘመናዊ ማሽነሪዎችን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉም ያደርጋል።
ይሄም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሞያዎችን አቅም በማሳደግ የንግድ እንቅስቃሴውን ለማነቃቃ ትልቅ መሰረት ይጥላል።
ፕሮጀክቱን ለማስጀመር 500 ሚሊየን ብር በጀት እንደተያዘም የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ እንደገለፀው፣ ግንባታው ሁለት ዓመት የሚፈጅ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ እና አጎራባች ሸገር ከተማ ወጣቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

ፕሮጀክቱ የቴክኖሎጂ ወርክሾፖችን እና ማሽነሪዎችን፣ መማሪያ ክፍሎችን፣ የአስተዳደር ሕንጻዎችን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሁም አረንጓዴ ቦታዎችን እንዳካተተም ተገልጿል።
ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ኮሌጁን የሚያስገነባው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት፣ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተቋማትን ገንብቶ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
በየሻምበል ምህረት