ከችግኝ ተከላ እስከ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ፡ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለዓለም ያበረከተው የአካባቢ ጥበቃ አርአያነት

You are currently viewing ከችግኝ ተከላ እስከ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ፡ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለዓለም ያበረከተው የአካባቢ ጥበቃ አርአያነት

AMN- ሰኔ 26/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በ”መደመር” እሳቤ እያካሄደች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት የተጀመረ ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።

ይህ መርሐ ግብር በሀገር ውስጥ ካለው ጠቀሜታ ባለፈ ፣ ለቀጣናው እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ትልቅ ተሞክሮ እና አርአያነትን አበርክቷል።

ኢትዮጵያ ከህፃናት እስከ አዛውንት፣ ከመንግስት ሰራተኞች እስከ ግል ባለሀብቶች ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን በአንድ ቀን በማስተባበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል እንደሚቻል በተግባር አሳይታለች።

ይህ ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ሌሎች ሀገራት ህዝባቸውን ለአካባቢ ጥበቃ እንዴት ማነሳሳት እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ ሆኗል።

ይህ ዓይነቱ እቅድ በትክክለኛ አመራር እና የህዝብ ተነሳሽነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መስራት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዛፍ የመትከል ሥራ ብቻ አይደለም።

ከተተከሉት ችግኞች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ እንጆሪ ያሉ የፍራፍሬ እና የቡና ተክሎች በመሆናቸው መርሐ ግብሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ገቢ ለማሳደግ ያለውን ጠቀሜታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አዲስ እይታ መስጠቱን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር የማይበግረው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት ማለትም ለጅቡቲ፣ ለሱዳን፣ ለደቡብ ሱዳን፣ ለኬንያ እና ለሶማሊያ በማጋራት የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል የቀጣናዊ ትብብር ተሞክሮን በተግባር አስተዋውቃለች።

በመርሐ ግብሩ አማካኝነት በአጭር ዓመታት ውስጥ የሀገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል።

ይህ ተሞክሮ የተራቆቱ መሬቶች ዳግም እንዲያገግሙ እና የከርሰ ምድር ውሃን ማበልጸግ እንደሚቻል ለዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች ትልቅ ማረጋገጫ ሆኗል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ትላልቅ የገንዘብ በጀቶችን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ፣ በ”መደመር” እሳቤ በውስጥ አቅምና በህዝብ አንድነት ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ለዓለም ያሳየ አዎንታዊ ተሞክሮ ሆኗል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review